"ዘማቾችና የዘማች ቤተሰቦች የኢትዮጵያ የምንግዜም ባለዉለታዎች ናቸዉ" ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ

 

**************************************************************

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የማህበራዊ ችግር ላለባቸዉ 99 ዘማቾች እና የዘማች ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤት ቁልፍ እና ከ1450 በላይ ለሚሆኑ የዘማች ቤተሰቦችና ዘማቾች ደግሞ የገና በአልን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ስጦታዎችን አበረከተ፡፡በቁልፍ ርክክቡና ስጦታዉ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የዘማች ቤተሰቦች ዉድ ህይወታቸዉንና የተለያዩ አካላቸዉን ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት የሰጡ የጀግና ልጆች ቤተሰቦች በመሆናቸዉ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ስናስብ ሁሌም የምናስባቸዉ ባለዉለታዎች ናቸዉ ብለዋል፡፡

''እናንተ ዘማቾች እና የዘማች ቤተሰቦች እርዳታ ሳይሆን የሚሰጣችሁ እናንተ ሀገርን ከመፈራርስ ስለረዳችሁ ልናመሰግናችሁ ነው'' ብለዋል።

አገሪቷም ባላት ሃብት ሁሉ ቅድሚያ በመስጠት የምትደግፈዉና የምታበረታታዉ እነዚሁኑ ጅግኖችና ቤተሰቦቻቸዉን ነዉ ብለዋል፡፡ የአካል መቁሰልና ሞት በማንኛዉም ተራ ምክንያት ሊከሰት የሚችል ክስተት መሆኑን ያነሱት ክብርት ከንቲባ ለአገር ሉአላዊነት መስዋዕት መሆንና የአገርን ክብር ለማስጠበቅ ዋጋ መክፈል ዘላለማዊ ኩራት ነዉ ብለዋል፡፡በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉ የዲያስፖራ አባላትም ለነዚህ የአገር ባለዉለታዎች ለማክበርና ከጎናችሁ ነን ለማለት ላደረጉት ድጋፍ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለዘማች ቤተሰቦች የሚያደርገዉን ድጋፍም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

Share this Post