ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷው አቅም ልትፈታው ይገባል

የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ በመከረው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ከቋሚና ተለዋጭ አባል አገራት ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷው አቅም ልትፈታው ይገባል ብለዋል። በተለይ ሩሲያ እና ህንድ አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ተላልፎ በአጎራባች የአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ የፈጸመውን ግፍ አውግዘዋል። ሩስያ በተወካዩዋ በኩል "ሰኔ ላይ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠና አቅም ያለው መንግስት በኢትዮጵያ ስላለ ችግሩን ራሳቸው ኢትዮጵያውያን ይፈቱታል" ብላለች።

ቻይና በበኩሏ"በሰብአዊ እርዳታ ስም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጣስ መሞከርን ቻይና በፍፁም አትቀበለውም፤የአለም ሀገራት በሙሉ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን ሊሆኑ ይገባል፤ ኢትዮጵያ ችግሯን ለመፍታት ራሷ በቂ ነች፤ በእርዳታ ስም ችግር ለመፍጠር የሚሞክሩ ቡድኖች የተመድን ህግ ሊያከብሩ ይገባል" በማለት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንደምትቆም አስታውቃለች።

የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ያስታወቀችው ህንድ ደግሞ፣ "ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስት በቂ ነው" ብላለች። ኬንያም ኢትዮጵያ ላይ ለመጣል የሚታሰብ ምንም አይነት ማዕቀብ እንደማትደግፍ አመልክታለች።

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሞከሩት የአሜሪካና እንግሊዝ ሀሳብ ኢትዮጵያ ችግሯን ለመፍታት በምታደርገው ጥረት የውጭ ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም በሚል በሌሎች አገራት በተነሱ ሀሳቦች ተቃውሞ ቀርቦበታል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው ልወስንልሽ የሚሉ የውጭ ኃይሎችን እንደማትቀበል በስብሰባው ላይ አስረግጠዋል።

Share this Post