“ አሁን ገንዘብ ሳይሆን ሀገር እና ህዝብ የምናተርፍበት ጊዜ ነው”

ምክትል ከንቲባ / አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የኢኮኖሚ አሻጥር እና ህገወጥ ተግባራት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በስራ ላይ ያለው የቁጥጥር ግብረሃይል በዛሬው ዕለት የስራ አፈጻጸሙን ግምገሟል፡፡ግብረሃይሉ ባለፉት ቀናት ባካሄደው የክትትል እና የቁጥጥር ስራዎች በአጠቃላይ የግብይት ስርዓቱን ማረጋጋት ተችሏል ያሉት የቁጥጥር ግብረሃይሉ ሰብሳቢ ምክትል ከንቲባ / አዳነች አቤቤ በተለይ መሰረታዊ የምግብ እና የፍጆታ እቃዎች አቅርቦትን በማሻሻል የገበያ ዋጋ እንዲረጋጋ አበረታች እና ተስፋ ሰጪ ውጤት ተገኝተዋል ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ አሻጥርን በመፍጠር ለረጅም ጊዜያት በህገ ወጥ መንገድ የተለያዩ አይነትና መጠን ያላቸው የብረታብረት እና የምግብ ምርቶችን ባከማቹ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ በቁጥጥር ስር መዋሉን ምክትል ከንቲባዋ ጠቁመዋል ፡፡ከዚህ ባለፈም የከተማዋን ሰላም እና ጸጥታን ለማናጋት በማሰብ ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ በርካታ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ ተግባራዊ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል ፡፡

እነዚህ ውጤቶች ቢገኙም አሁንም ህገወጥነትን በመቆጣጠር ፤የኢኮኖሚ አሻጥሩን በዘላቂነት መግታት ፣ሌብነት፣ መልካም አስተዳደር ፣የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ የሚያውኩ እና ጫና የሚፈጥሩ ተግባራትን ከመፍታት እንጻር አሁንም በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩ / አዳነች አቤቤ አመልክተዋል

ከፌደራል ጀምሮ በከተማ እና በአጎራባች ከተሞች የተዋቀረው ግብርሃይል የቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የህብረተሰቡ ተሳትፎ እና ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የጠቀሱት ምክትል ከንቲባዋ በከተማዋ የሚታየውን ማንኛውንም ህገወጥ ተግባር ለመከላከል የጥቆማ መስጫ ምቹ ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ /ቤት የጥቆማ መስጫ አድራሻዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

በዚሁ መሰረት 9977 በነጻ የስልክ መስመር እና በከንቲባ /ቤት አራተኛ ፎቅ በአካል በመቅረብ ጥቆማ መስጠት የሚቻል ሲሆን የጥቆማ አቀራረብ ፣የማበረታቻ ስርዓት እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ የከተማ አስተዳደሩ ያወጣውን ዝርዝር ደንብ እና መመሪያ በቀጣይ የሚቀርብ ይሆናል፡፡

Share this Post