የለመለመች ኢትዮጵያን ለትውልድ የማስረከብ ሃላፊነታችንን እንወጣ።" - አቶ ጥራቱ በየነ

 

በአዲስ አበባ በዘንድሮው አራተኛው የአረንጓዴ አሻራ የማኖር መርሐግብር እስካሁን 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል ፤ በዚህም የእቅዱን 76 በመቶ ማሳካት ተችሏል ።

ከህዳሴው ግድብ የሶስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት አፈፃፀም ጎን ለጎን ለአራተኛው ዙር የችግኝ ተከላ ስኬት ነዋሪው በጋራ በመረባረብ ታሪካዊ ለትውልድ የሚተላለፍ አሻራ የማኖር ሃላፊነቱን እንዲወጣም በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ጥራቱ ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐግብር አፈፃፀምን በገመገሙበት ወቅት በከተማዋ በቅርቡ በአንድ ጀምበር 4 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ለተያዘው እቅድ ስኬት ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት በአፋጣኝ ሊያጠናቅቁ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።

በከተማዋ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፀጥታ አካላት፣ ወጣቶችና ሴቶች ፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ፣ በጎ ፈቃደኞች፣ የሲቪክ ማህበራት ባለሃብቶችና ሁሉም ዜጎች የአረንጓዴ አሻራቸውን ከባለፉት ጊዜያት በተሻለ በማኖር የለመለመች ኢትዮጵያን ለትውልድ የማስረከብ ሃላፊነት እንዲወጡ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል ።

 

 

Share this Post