07
Dec
2023
*
የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀምና አተገባበር ዙሪያ ለክፍለ ከተማና ለማዕከል የዘርፉ ባለሙያዎች እና ቡድን መሪዎች ሙያዊ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሁሴን ዝናብ ከተማችን አዲስ አበባን የሚመጥን የኮሙኒኬሽንና የተግባቦት ስርዓት ለመዘርጋት ንቁ የዲጂታል ሚዲያ ሰራተኛ መፍጠር እንደሚገባ ገልፀዋል።
አቶ ሁሴን አክለውም የዲጅታል ሚዲያን ለበጎ አላማ በመጠቀም ለሃገርና ትውልድ ግንባታ ለማዋል የዘርፉ ተጠቃሚዎች ተግተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል። እኛነታችንን ይበልጥ አጋምደው የአብሮነት ውርሳችንን ሊያሰፉና ሊያጠናክሩ እንዲሁም ለሀገር ሰላም ና ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ በትግሉ ኪታባ በበኩላቸው ስልጠናው ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆይ መሆኑን ጠቅሰው በዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ በበቁና ልምድ ባካበቱ ምሁራን የሚሰጥ ሙያዊ ስልጠና ስለሆነ በትኩረት መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል።