የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እርምጃውን እየወሰደባቸው ያሉት ተግባሩ ይፈፀምባቸዋል ተብሎ በተጠረጠሩና ጥቆማ በተሰጠባቸው ሆቴሎች፣ ባሮችና ሬስቶራንቶች ሲሆኑ ከህብረሰቡ ለሚደርሰው ጥቆማ ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጋር በቅንጅት በመሰራትም ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
ቢሮው እንደ ገለፀው፣ ከነባሩ የሀገራችን ባህል ፣ ወግ፣ የአኗኗር ስርዓት እና ኃይማኖቶች ባፈነገጠ መልኩ የግብረ-ሰዶም ተግባር በሚያስፈጽሙ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ፔንሲዮኖችና መሰል የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከህብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ መሰረት አስተማሪ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የግብረ-ሰዶም ተግባር መፈጸምና ማስፈጸም በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ባሉ ሕጎች የተከለከለ መሆኑን ገልፆ ይህንን አስጸያፊ በሰውም በአምላክም ዘንድ የተጠላ ድርጊት በሚፈጽሙና በሚያስፈጽሙ የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቆማት ላይ ካለ አንዳች ርህራሄ ከህብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ መሰረት ከፖሊስ ጋር በመተባበር እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
በዚሁ መሰረት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 አስተዳደር ውስጥ በሚገኝ "አበባ ገስት ሐውስ" በሚባል የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቋም ላይ ከህብረተሰቡ ለሰላምና ፀጥታ ቢሮ በደረሰ ጥቆማ መሰረት እርምጃ የተወሰደበት ሲሆን የተቋሙን ኃላፊ በከተማው ፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውል በማድረግ ምርመራ እየተከናወነበት ይገኛል።
ከግብረሰዶም ፀያፍ ተግባር ጋር የተገናኘ መረጃ እና ጥቆማ ያለው ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በግንባር በመቅረብ እንዲሁም በነፃ የስልክ መስመር 991 እና 987 እንዲሁም በ011-1- 11-01-11 እና 011-5-52-63-02 በመጠቀም መረጃና ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ከዚህ ቀፊትም የተገለፀ ሲሆን አሁንም ህብረተሰቡ ይህንኑ አጠናክሮ እንዲቀጥሌ ተጠይቋል።
በሚደርሰው ጥቆማ መሰረትም ቢሮው የማያዳግም እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።