ከሁለት መቶ ሚሊየን ብር በላይ በጀት ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተመረቁ፡፡

የካ ክፍለ ከተማ በሁለተኛው ዙር 90 ቀናት በሰው ተኮር ዕቅዱ ያስገነባቸውን የህብረተሰቡን ችግር እንደሚያቀሉ ተስፋ የተጣለባቸውን 10 ፕሮጀክቶችን አስመረቀ፡፡

ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት በከተማችን 14 የሆነው የምገባ ምዕከል፤ የዳቦ ፋብሪካ በሶስት ትምህርት ቤቶች ተጨማሪ የመማርያ ክፍሎች ያሏችው ባለ 4 ወለል ህንጻዎች የመማሪያ ክፍሎች የስፓርት ማዘውተሪያና ሱቆች መሆናቸው ታውቆአል::

ፕሮጀክቶቹን መርቀው የከፈቱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማ አስተዳደሩ የኅብረተሰቡን የኑሮ ጫና ለማቅለል በገባው ቃል መሰረት የወገን አለኝታ የሆኑ ባለሀብቶችንና ህብረተሰቡን በማስተባበር የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገለጸዋል፡፡

14ኛው ምገባ ማእከል ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን የዕለት ጉርስ ማግኘት የተሳናቸው እስከ 1200 ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ የሚመገቡበት መሆኑም ታውቋል፡፡

በአቅራቢያው የሚገኙ አርሶ አደሮችም ለሶስት ወራት በምግባ ማዕከሉ ማእድ እንደሚያጋሩም ታውቋል፡፡

ማእከሉን መርቀው የከፈቱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ስራዎቻችን ለሰው ልጅ ቅድሚያ የሚሰጡ መሆን አለባቸው የምንለው በተግባር መሆኑን በየካ ከፍለ ከተማ የተገነቡ 10 ፕሮጀከቶች ማሳያዎቻችን ናቸው ብለዋል፡፡ ቅን ልቦና ያላቸው ባለሀብቶች ካተረፉት ለወገኖቻቸው በማካፈል ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግም ችለናል ብለዋል፡፡

ሌላው ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የዳቦ ፋብሪካ በቀን እስከ ስድስት መቶ ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን 150 ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሞገስ አባተ ገልጸው ፋብሪካው በአነስተኛ ዋጋ ዳቦ ለገበያ ከማቅረቡ ባሻገር 100 አቅመ ደካማ ነዋሪዎች በየቀኑ በነጻ ዳቦ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ከለወጡ በፊት ከሶስት መቶ ሺህ ያልበለጠ የነበረው የዳቦ አቅርቦት ከተማ አስተዳደሩ ለባለሀብቶች ተገቢውን ድጋፍ በማድረጉ አቅርቦቱ ከሶስት ሚሊዮን በላይ በማድረስ መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡

ተጨማሪ የመማሪ ክፍሎች በሶስት ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ተጨማሪ የመማርያ ክፍል ህንጻዎች ሲሆኑ የተማሪ ክፍል ጥምርታውን በማሻሻል በአንድ ክፍል ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎቸን 50 ማድረስና የፈረቃ ትምህርትን ማስቀረት በማስቻሉ ለትምህርት ጥራት መሻሸል አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

ትምህርት ትውልድ መገንቢያ በመሆኑ የላቀ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ህዝቡ ትምህርት ቤቶችን በባለቤትነት እንዲጠብቅና እንዲንከባበከብ አሳስበዋል፡፡

በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው 60/90 ቀናት ዕቅድ በሕብረተሰቡ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ያስቻሉ በመሆኑ ተሞክሮውን ቀምረን በማስፋት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ገልጸው በዚህ ስራ ላይ እየተሳተፉ ያሉትን ባለሀብቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች አመስግነዋል፡፡

 

Share this Post