የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የ2015 ዓ.ም የስድስት ወራት የስራ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ከተቋሙ ባለሙያዎችና አመራሮች ጋር በቅንጅት በማከናወን ቀጣይ የስድስት ወራት የስራ አቅጣጫ አስቀመጠ።
በስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም መክፈቻ ላይ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን ዝናብ እንደተናገሩት ባለፉት ስድሰት ወራት በከተማ ደረጃ ያከናወናቸውን የኮሙዩኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ስራዎቻችንን በጥልቀት በመገምገምና የሚስተዋሉ ውስንነቶችን በመለየት በቀጣይ በቅንጅት የላቀ ትኩረት ሰጥተን በመስራት ተቋማችን በከተማና በሀገር ግንባታ ላይ የሚያሳድረውን አዎንታዊ ተጽዕኖ በማጎልበትና ቢሯችን በሕዝብ ዘንድ የሚኖረውን ሁለንተናዊ ተቀባይነት ማሳደግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ምክትል ኃላፊው አክለው እንደተናገሩት በከተማ ደረጃ የኮሙዩኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን በተሻለ አጠናክሮ በማስቀጠል በሕዝብና በመንግስት መካከል የሚያጋጥምን የመረጃ ክፍተት በመድፈን ቢሮው ድልድይ ሆኖ ዘርፈ ብዙ ስኬት በሁሉም ረገድ እንዲያስመዘግብ ሁላችንም የተጣለብንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይጠበቅብናል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ሕዝብን በከተማ ደረጃ በሰው ተኮር ዕቅዶችና በመሰል ተግባራት ላይ በማንቀሳቀስ በዘመቻ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ያመላከቱት አቶ ሁሴን በሚቀጥሉት ስድስት ወራትም በይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል ።
የአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የሚዲያ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ መንግስቱ ገብሬ በበኩላቸው አጠቃላይ በቢሮ ደረጃ የሚተገበሩ ዕቅዶችን መከለስና አፈጻጸማቸውን በየግዜው እየመዘኑ መጓዝ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል ።
ቢሮው ባለፉት ስድስት ወራት በከተማ አቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ በማህበራዊ ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ያከናወናቸውን ቁልፍ ተግባራትን ጨምሮ በየግዜው አጀንዳ ሆነው በሚያጋጥሙ ጉዳዮች ዙሪያ ብዥታን ለማጥራት የተሰሩ የኮሙዩኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን እንዲሁም አፍራሽ ተልዕኮዎችን ለመመከት የተከናወኑ ተግባራት በጥልቀት የተገመገሙ ሲሆን በቀጣይ በይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ተግባራት በውይይት ተለይተው የጋራ አቅጣጫ ተቀምጦባቸዋል።
በሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንዲከናወኑ ተለይተው የትኩረት አቅጣጫ ተደርገው የተቀመጡ የኮሙዩኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ለማስፈጸም ከመግባባት የተደረሰ ሲሆን አጠቃላይ የቢሮው ዕቅዶች በሚፈለገው ደረጃ ውጤት እንዲያመጡ ቅንጅታዊ አሰራርን መከተል እንደሚያስፈልግ በግምገማው ወቅት ተመላክቷል። የከተማውን ማህበረሰብ ሀሳብ እና ጥያቄዎች እንዲሁም ቅሬታዎችን ማስተናገድ ና የሚመለከተው ተቋም የመፍትሄ አካል በመሆን ምላሽ የሚሰጥበት የተሳለጠ የተግባቦት አካሄድ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት በውይይቱ የተነሳ ሲሆን የሰው ሀይል እጥረትም ለመቅረፍ ታቅዶ እየተሰራ ስለመሆኑ ምላሽ ተሰቷል::