የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በልዩነት ለተፈጠረው የኤሌክትሪክ ኃይል እና የውሃ መቆራረጥ በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከሰሞኑ የተከሰውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ዶ/ር ገበየሁ ሊከሳ ገልፀዋል።
ለኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጡ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም በጣለው ከባድ ዝናብ መዲናዋ ካሏት 137 መጋቢ መስመሮች ውስጥ በ50ዎቹ ላይ ከባድ ጉዳት በመድረሱ እንደሆነም ተጠቁመዋል።
በተጨማሪም በግንባታ ፕሮጀክቶችና በአረጁ መስመሮች የማከፋፋያ ጣቢያ ጥገና እና በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ተደጋጋሚ ስርቆቶች ለኤሌክትሪክ መቋረጡ በምክንያትነት አንስተዋል።
በተደረገው ፈጣን የጥገና ሥራም የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር በአብዛኛው አካባቢ መፈታቱን ሃላፊው ገልፀዋል።
ዳግም በሀይል አቅርቦት ላይ የመቆራረጥ ችግር እንዳይፈጠር መስመሮችንና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የመጠገንና የግንባታ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ የውሃና ፍሳሽ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ዘለቀ እንደተናገሩት በአቅርቦት እና ፍላጐት አለመጣጣም እንዲሁም ከሰሞኑ በተፈጠረው የኤሌትሪክ ሀይል መቆራረጥ ምክንያት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ውሃን በፈረቃ ተደራሽ ለማድረግ መገደዳቸውን ገልፀዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የሁለቱ መስሪያ ቤቶች ባለፈው ሳምንት በኤሌክትሪክ ኃይል እና ወሃ መቆራረጥ ለተፈጠረው ችግር ህብረተሰቡን ይቅርታ ጠየቀዋል፡፡