ለህዝብ የተገባን ቃልኪዳን በማክበር እና ወደ ተግባር በመግባት ረገድ በከተማችን በ60/90 ቀናት በርካታ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለህዝብ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ተችሏል።
በዛሬው ዕለትም በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በ90 ቀናት የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነን ጨምሮ የተለያዩ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በቦሌ ክፍለ ከተማ ከ323 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የ90 ቀናት ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን ማስመረቅ ተችሏል።
ዛሬ የተመረቁት 85 ፕሮጀክቶች በከተማ አስተዳደሩ፣ በክፍለ ከተማው፣ በግል ባለሃብቱና በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተገነቡ ናቸው።
በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ የልማት ፕሮጀክቶቹ ለስራ እድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነቱ የፈጠረውን የኢኮኖሚ ጫና ለማስታገስ፣ ለከተማዋ ገጽታና ለወጣቶች ስብዕና ግንባታ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
ባለፉት 90 ቀናት የመንግስትን አገልግሎት አሰጣጥ የተሳለጠና ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ የህንጻዎች እድሳት መከናወኑም ተጠቅሷል።
የተቋማት አሰራር በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።
የተመረቁት ፕሮጀክቶችም፥ ለአቅመ ደካሞች የሚውሉ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የሸገር ዳቦና የአትክልት መሸጫ ሱቆች፣ የምገባ ማዕከላት፣ የከብትና የዶሮ ርባታ ሼዶች፣ የአደባባይ ማስዋብ ፣ የልጆች መጫወቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ጨምሮ ሌሎች በዘጠና ቀናት እቅድ የተከናወኑ ስራዎች ናቸው።