ከንቲባ አዳነች አቤቤ በህብረት ስራ ማህበራት የሚሰራን የጋራ መኖርያ ቤት ግንባታ ዛሬ አስጀምረዋል፤

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ / አዳነች አቤቤ የከተማችንን የቤት ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም መንግስት እየሰራ ካለው በተጨማሪ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም የግድ ነው ያሉ ሲሆን ከለውጡ በኋላ መንግስት አዲስ ስትራቴጂ በመቅረፅ በመንግስትና በግል ትብብር እንዱሁም በማህበራት የሚገነቡ ቤቶችን እንደ አማራጭና ስትራቴጂ ዘርግቷል ብለዋል።

ከንቲባዋ አክለውም የከተማችንን የቤት አቅርቦትና ፍላጎት ለማቀራረብ በኮንዶሚኒየም፣ በሪል-ስቴትና በማህበራት እስካሁን ብዙ ቢሰራም እስካሁን በተፈለገው ልክ ሊጣጣም ባለመቻሉ ዛሬ ያስጀመርነው አማራጭ ትግበራም እጅግ በጣም ጠቃሚ ሆኖ እናገኘዋለን ብለዋል።

በማህበራት ተደራጅተው የጋራ መኖርያ ቤቶችን ለማልማት ለሚመጡ አካላት የከተማ አስተዳደሩ መሬት ያቀርባል፣ ስታንዳርድ ዲዛይን ያቀርባል፣ የተሻሉ ኮንትራክተሮችንም በመምረጥ ለማህበራቱ ያዘጋጃል እንዲሁም የክትትልና ድጋፍ ስራም ይሰራል ሲሉም አክለዋል።

መንግስት ብቻውን በመስራት የከተማችን የቤት ፍላጎት ሊሳካ አይችልም ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ሁሉንም ዜጋም የቤት ባለቤት ማድረግ አይቻልም። በተለይ ለኮንዶሚኒየም ቆጣቢዎች የማህበራት አማራጭ ከተማ አስተዳደሩ የሚፈልገውና የሚያበረታታው መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።

ዛሬ የግንባታ ማስጀመርያ መርሃ-ግብር የተካሄደበት 54 ማህበራት ስር የታቀፉ 4000 በላይ ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሲሆን G+9 እና G+13 የመኖርያ ህንፃዎች እንደሚኖሩት ተገልጿል።

Share this Post