ከንቲባ አዳነች አቤቤ

"ዛሬ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ የተገነቡትን 70 በላይ የመሸጫ ሱቆች የተካተቱበት የአቃቂ ሰብል ምርት ገበያ ማዕከልን እና 140,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሰፈረውን የእንስሳት ልማት ልህቀት ማዕከልን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል።

ህዝባችንን በብርቱ እየፈተነ ያለውን የኑሮ ጫና ለማቃለል ከጀመርናቸው ስራዎች መካከል አንዱ የሆነው የሰብል ምርት ገበያ ማዕከል፣ ህብረተሰቡ በቀጥታ ከአምራቹ እንዲሸምት የሚያስችለው እና ገበያውን በማረጋጋት ትልቅ አስተዋፅዖ ያለው ነው።

የምርት ገበያው ሱቆችን ጨምሮ መጋዘን፣ ወፍጮ ቤት እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት የተካተቱበት ሲሆን ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ አምራቾች እና አርሶአደሮች የስራ እድል ይፈጥራል።

የእንስሳት ልህቀት ማዕከሉ ደግሞ የዶሮና የወተት ላም እርባታ፣ የከብት ማደለብ፣ የመኖ ማቀነባበሪያ እንዲሁም የምርት ማሳያና መሸጫ ቦታዎችን ያካተተ ነው።

ይህ የልህቀት ማዕከል በዘርፉ ለሚሰማሩ 485 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን የእዉቀት፣ የክህሎት፣ የምርምር፣ የግብዓት፣ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምንጭ ሆኖ ያገለግላል።

የነዋሪዎቻችንን የኑሮ ጫናዎች ለማቃለል እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በታማኝነትና በትጋት መስራታችንን እንቀጥላለን"

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ

Share this Post