የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ዓመት መዳረሻ በሆኑት ስድስቱ የጳጉሜን ቀናት ከተማ አስተዳደሩ የሚያከናውናቸውን መርሃ-ግብሮች አስመልክቶ ዛሬ ለሚዲያዎች መግለጫ ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናትአለም መለሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የጰጉሜን ቀናት ከፌዴራል መኔግስት ከወረዱ የጋራ እቅዶች ጋር በማጣጣም በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃም በደማቅ እና በተስፋ ሰጪ መርሃ-ግብሮች ይከናወኗል ብለዋል።
በዚሁ መሰረት ጳጉሜን አንድ የአገልጋይነት ቀን፣ ጳጉሜን ሁለት የመስዋዕትነት ቀን፣ ጳጉሜን ሦሰት የበጎነት ቀን፣ ጳጉሜን አራት የአምራችነት ቀን፣ ጳጉሜ አምስት የትውልድ ቀን እንዲሁም ጳጉሜ ስድስት የአብሮነት ቀን ሆነው በልዩ ልዩ መረሃ-ግብሮች እየተከበሩ ይውላል ብለዋል።
የቢሮ ኃላፊዋ በእያንዳንዱ የጲጉሜን ቀናት የሚተገበሩ ዝርዝር መረሀ-ግብሮችን አስመልክተው እንደሰጡት ማብራሪያ መሰረት በጳጉሜን አንድ "የአገልጋይነት ቀን" ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ የህንጻ ምርቃት፣ በ33 ወረዳዎች የተገነቡ የስማርት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ክፍት ማድረግ፣ ለአንጋፋ መምህራን ዕውቅና መስጠት፣ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎትና ለጤና ባለሙያዎች በዕለቱ ዕውቅና እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በጳጉሜ ሁለት "የመስዋዕትነት ቀን" በሁሉም የመንግሥትና የግል ተቋማት ሰንደቅ-ዓላማ በመስቀል ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና የጸጥታ አካላትን ማመስገን፣ በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ የፓናል ውይይት፣ በሁሉም ከፍለ ከተማና ወረዳ እንዲሁም ተቋማት የደም ልገሳ መርሃ-ግብር እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
ጳጉሜ ሦስት በሚውለው "የበጎነት ቀን" 860 ቤቶችን ለአቅመ -ደካሞች ማስተላለፍ፣ ለ3000 ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የማዕድ ማጋራት በከተማ ደረጃ ማከናወን፣ በሁሉም ክፍለ ከተማና ወረዳ የማዕድ ማጋራት ማድረግን ጨምሮ ቀጨኔ አካባቢ የተገነባው 20ኛው የተስፋ-ብርሃን የምገባ ምዕከል ምርቃት እንደሚከናወን የቢሮ ኃላፊዋ ይፋ አድርገዋል።
ጳጉሜ አራት በሚውለው "የአምራችነት ቀን" የሀገር ውስጥ ምርቶች ባዛርና ኤግዚቢሽን ፤የአያት የገበያ ማዕከል ምርቃት፣ አምራችነት የሚያበረታቱ ልዩ ልዩ መሰናዶዎችን በሚዲያ ተደራሽ ማድረግን የሚያካትት እንደሚሆን ተመላክቷል።
ጳጉሜ አምስት በሚውለው "የትውልድ ቀን" የመምህራን እና የወላጆች የውይይት መድረክ፣ አብሮነትን ለማጠናከር የሚረዳ የማስ እስፖርት፣ የወላጅ አልባ ህጻናት ርክክብ በማዘጋጀ ቤት መፈጸምን ጨምሮ ለትውልድ ሁለተናዊ ዕድገት ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን በሚዲያ ተደራሽ ማድረግን የሚያጠቃልል ይሆናል ብለዋል።
በተመሳሳይ ጳጉሜ ስድስት በሚውለው "የአብሮነት ቀን" በሁሉም ክፍለ ከተማና ወረዳ አብሮነትን ማዕከል ያደረጉ ውይይቶች፣ አብሮነትና ወንድማማችነትን የሚያጎሉ የሚዲያ ፕሮግራሞችን ጨምሮ የዋዜማ የመዝናኛ ሙዚቃ ኮንሰርት እንደሚከናወን ወ/ሮ እናታለም መለሰ በመግለጫቸው ወቅት አስታውቀዋል።