የጋራ መሰባሰቢያ ጎጇችን በሆነችው አዲስ አበባ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ከተማችንን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ለተጨማሪ ዕድገት የምንጠቀምበት ሊሆን እንደሚገባ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለፁ።
አቶ ሞገስ ባልቻ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክ/ከተሞችና ወረዳዎች ደረጃ እየተካሄደ የነበረው የኢሬቻ በዓል የፓናል ውይይት ኘሮግራሞች ዛሬ መጠናቀቃቸውን ተከትሎ እናዳሉት፥ የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ፣ አምሮና ተውቦ፣ ሰላምና መተሳሰብ ተነግሮበት፣ ፍቅርና መረዳዳት ተመክሮበት ይከበራል ብለዋል።
አቶ ሞገስ አክለውም፣ ኢሬቻ የፍቅርና የሰላም እሴት ማሳያ፣ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ታላቅ የምስጋና በዓል እና የሰው ልጆች በእኩልነት የሚያከብሩት የሰላምና የፍቅር በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፣ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ስርዓት አንዱ አካል የሆነ ህዝባዊ በዓል ነው እንዲሁም ክረምቱ አልፎ ብራ ሲሆን ተፈጥሮን የፈጠረ ፈጣሪ የሚመሰገንበት የምስጋና በዓል በመሆኑ የዘንድሮው የኢሬቻ በዓልም እሴቱን ጠብቆ በከተማችን እንደሚከበር ገልፀዋል።
የኢሬቻ በዓል በንጽሕና ፈጣሪን ምህረት የሚጠይቅበት፣ መጪውን ጊዜ የሰላምና ፍቅር እንዲያደርግ ፈጣሪ የሚለምንበት በዓል ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር፥ የከተማችን ነዋሪዎች በአምስቱም የከተማችን መግቢያና መውጫ በሮች እንግዶችን በተለመደ ኢትዮጵያዊ ባህል እንዲቀበል አሳስበዋል።
አሁን አሁን ከአመት አመት የሚናፈቁና በጉጉት የምናከብራቸው የአደባባይ በዓላት ቱሪስቶች ሩቅ ሳይሄዱ የኢትዮጵያን መልክ እዚሁ በመዲናችን ማግኘትና መጎብኘት ጀምረዋል ያሉት አቶ ጃንጥራር፣ ነዋሪዎቿም በእነዚህ በዓላት ከመዋብና ከማጌጥ አልፈው የገቢ ምንጭ ጭምር እያደረጓቸው ነው ብለዋል።
በማጠቃለያ መድረኩ ላይ ከ11ዱም ክፍለ ከተሞች ተወክለው የተገኙ ታዳሚዎችም፣ ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ በዓል ብቻ አለመሆኑን ገልፀው፣ የሁሉም በዓል የሆነው ኢሬቻ በሰላም እንዲጠናቀቅ የከተማችን አምባሳደር እንሆናለንም ሲሉ ገልፀዋል።