የከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት‼️

ዛሬ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ልምዳችንን በአገር አቀፍ ልምድ ልውውጥ መድረክ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አረጋ ከበደ፣ የሲዳማ ብሔራዊ ክልልዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ ሚኒስትሮች፣ የኦሮሚያና የድሬዳዋ ከተማ አመራሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም የመስኩ ባለሙያዎች በተገኙበት ልምዳችንን ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች አካፍለናል።

ባለፉት 2 ዓመታት ለትውልድ ግንባታ ትኩረት ሰጥተን፣ የአስፈጻሚ ተቋማትን ቅንጅት ፈጥረን፣ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተን በአሰራርና በአደረጃጀት ስራውን መርተናል።

በዚህም ወላጆችንና አሳዳጊዎች በዕውቀት ሕጻናት እንዲያሳድጉ 2500 የቤት ለቤት ተንከባካቢዎችን አሰልጥነን አሰማርተን፣ 56 ጤና ጣቢያዎችንና 46 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን አሸጋግረን፣ 152 መዋለ ህጻናትን እና 156 የመጫወቻ ስፍራዎችን ገንብተን አዲስ አበባ ከተማን የሕጻናት ማደጊያ ምርጥ አፍሪካዊ መዲና ለማድረግ በትጋት በመስራት ያካበትነውን ልምድ አጋርተናል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ለአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች ልምዳችንን ያካፈልን ሲሆን፣ የትውልድ ግንባታ ስራችን ( የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም) የሀገር አቀፍ ትኩረት እንዲሆን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ተወስኗል።

በስራዎቻችን ሁሉ ያልተቆጠበ ድጋፍ ያደረጉልንን ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በራሴና በከተማ አስተዳደራችን ስም ማመስገን እወዳለሁ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ

Share this Post