-
በዛሬው እለት በ2015 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የከተማ አስተዳደሩ ማበረታቻ ሽልማት ሰጥቷል።
የላቀ ውጤት አስመዝግበው የዕውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት ከክብርት ከንቲ አዳነች አቤቤ እጅ ከተቀበሉት ተማሪዎች መካከል በከተማ ደረጃ በተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 በላይ አማካይ ውጤት ያስመዘገቡ 97 ተማሪዎች ፤ በማህበራዊ ሳይንስ በአማካይ ውጤታቸው ከ450 በላይ ያስመዘገቡ 66 ተማሪዎች ፤ በማህበራዊና በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ በየደረጃው የላቀ ወጤት ያስመዘገቡ ስድስት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ፤ በተማሪዎች ውጤት የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ዘጠኝ ትምህርት ቤቶችና በከተማ ደረጃ የላቀ ውጤት የተመዘገበባቸው ሦስት ክፍለ ከተሞች ይገኙበታል።
ከንቲባ አዳነች በተማሪዎች የዕውቅና እና ሽልማት መርሃ-ግብሩ ላይ እንዳሉት በሁሉም ረገድ ለትምህርት መሻሻል በቅንጅት የሰራነው አበረታች ስራ ለፍሬ መብቃቱን በተጨባጭ ያየንበት ነው ያሉ ሲሆን፣ የዘንድሮው የተማሪዎች ውጤት ከአምናው በተሻለ በትምህርት ዘርፍ በትኩረት ከሰራን ከዚህም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደምንችል ተስፋ የሰጠን ነውም ብለዋል።
ትምህርት የሁሉም ነገር መሰረት እንደመሆኑ መስኩን የትኩረት ማዕከልና ቀዳሚ አጀንዳ አድርገን በመስራታችን በተመሳሳይ በ6ኛ እና በ8ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተከታታይ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ችለናልም ሲሉ ገልጸዋል።
በሚቀጥለው የከፍተኛ ትምህርት ምዕራፋችሁ በተመሳሳይ ተግታችሁ መስራትና መመራመር ላይ መዘናጋት ፈጽሞ የለባችሁም ሲሉ ያሳሰቡት ከንቲባ አዳነች፣ ትውልድ ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሀገር ግንባታችን ቁልፍ ተግባርም ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ፣ የካ ክ/ከተማ እና ቦሌ ክ/ከተማ የላቀ ውጤት በከተማ ደረጃ በማስመዝገብ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በመውጣት በከንቲባ አዳነች እውቅና የተሰጣቸው ክፍለ ከተሞች ናቸው።