"አካል ጉዳተኝነት አለመቻል ሳይሆን በውስጣችን ያሉ እምቅ ችሎታዎችን በጥበብ ለማውጣት ዕድል የሚሰጥ ነው" ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ከንቲባ አዳነች ይህንን ያሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ግዜ "ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ለዘላቂ ልማት ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር ያስፈልጋል" በሚል መሪ ሐሳብ በከተማ ደረጃ በተከናወነ የአካል ጉዳተኞች ቀን ላይ ነው።

ከተማችን የአካል ጉዳተኞችን ዘላቂ ልማትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲያስችላት በነደፈቻቸው አካታች ፖሊሲዎች ላይ የተቀመጡ መረሀ-ግብሮችን በቁርጠኝነት ደረጃ በደረጃ ትተገብራለች ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ አዲስ አበባ አካታችነቷን እና የብልፅግና ተምሳሌትነቷን የምታረጋግጠው አካል ጉዳተኞችንም በዘላቂነት ተጠቃሚ በሚያደርጉ ስራዎቿም ጭምር ነው ብለዋል።

ከለውጡ ማግስት አንስቶ አጠቃላይ በልማትና ዕድገት ፖለሲዎቻችን አካታች ሥራዎችን እያከናወንን ስለመሆናችን የአብርሆት ቤተ-መጽሀፍት ለአካል ጉዳተኞች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን አሟልቶ መገንባቱ ተጨባጭ ማሳያ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ጽ/ቤትንን ጨምሮ በሌሎችም የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የህንጻ ዲዛይን ማሻሻያና አካታች ስራዎችን እያከናወንን እንገኛለንም ብለዋል።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግስት በፈረማቸው በ17ቱም የልማት ግቦች ሁሉ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ አካታች እንቅስቃሴ እንዲደረግ መንግሥት ከመቼውም ግዜ በላይ የላቀ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ በአካል ጉዳተኞች እምቅ የውስጥ ችሎታ ላይ ማዕከል ያደረገ ጥናታዊ ጽሁፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዘርፉ ሙሁራን ተዘጋጅቶ ለፓናል ውይይት መነሻ ሆኖ ቀርቧል።

Share this Post