--------
"ቀጣይ ምዕራፍ ለሁለንተናዊ ለውጥ" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አማክኝነት የተዘጋጀ የምስጋናና የሰላም ኮንፈረንስ በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።
በኮንፍረንሱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት እያለፍን ያለነው በለውጥ ሂደት እንደመሆኑ በርካታ ፍሬዎችና ድሎችን ከህዝባችን ጋር ሆነን አስመዝግበናል ያሉ ሲሆን ያለ እናንተ ትብብርና ፀሎት አንድም የተገኘ ውጤት የለም ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች አክለውም፣ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፍን ለውጡን እያስቀጠልን እንደምንገኝ ሁሉ ፈተና በገጠመን ወቅት ሁላችሁም ኃይማኖቶች አገር እንድትቀጥል በተከታታይ ላደረጋችሁት የፀሎት መርሃ-ግብር መንግሥት ዕውቅና ይሰጣልም ብለዋል።
ወደ ሰላም መንገድ ለሚመጣ ኃይል ሁሉ የመንግሥት በር ሁሌም ክፍት መሆኑን ያረጋገጡት ከንቲባ አዳነች፣ ከግጭት ይልቅ ከእርቅ ፣ ከሰላምና አንድነት የምናተርፈው እጅግ ብዙ ነው ሲሉም አሳስበዋ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሼኽ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በሰላምና ምስጋና ኮንፈረንስ ላይባደረጉት ንግግር ሰላም ሲኖር ያቀድነውን ሁሉ ከግብ ማድረስ እንችላለን ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን በተገኘንበት ሁሉ በአንድነት ሁሉም ጉዳይ ወደ ወይይት፣ በምክክር ወደ ሚገኝ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲመጣ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
መርሃ-ግብሩ በዋነኛነት የህዝበ-ሙስሊሙ የዘመናት ጥያቄዎች ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በመንግስት በተገባው ቃል መሰረት በመመለሳቸው በየደረጃው ለህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን የማመስገን ሲሆን በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ህዝበ ሙስሊሙ ሚናውን የበለጠ እንዲወጣም ማድረግን ያለመ ነው።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የህዝበ ሙስሊሙ መሪ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ህጋዊ እውቅና ያለው ተቋም ሆኖ እንዲመሰረት እና ተቋማዊ አደረጃጀቱም እንዲሻሻል መደረጉ ምላሽ ካገኙ ጥያቄዎች መካከሎ አንዱ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።
በሼሪያ ህግ የሚመሩ ወለድ አልባ ባንኮች መመስረት እና በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ህዝበ ሙስሊሙ የሚያነሳቸው ለአምልኮና ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ቦታዎች ጥያቄ በየደረጃው መመለሳቸውም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ካገኛቸው የለውጥ ትሩፋቶች መካከል መሆናቸው ተገልጿል።
በመድረኩ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የፌደራልና የክልል መጅሊስ አመራሮች፣ ኢማሞች፣ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ አምባሳደሮች እና የተለያዩ ሀይማኖቶች መሪዎች ተገኝተዋል።
ለበለጠ መረጃ:-
👉YouTube https://youtu.be
👉Tik Tok https://www.tiktok.
👉Telegram https://t.me/AAcommu
👉Facebook https://www.facebook.com