"የህግ አግባብን ተከትለው በማይሰሩ የቤቲንግ ስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ መውሰድ ጀምረናል።" ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ

--------------

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የህግ አግባብን ተከትለው በማይሰሩ የቤቲንግ ስፖርት አጫዋች ድርጅቶች ላይ የከተማ አስተዳደሩ ስለ ወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ በሚመለከት በዛሬው እለት ለሚዲያ አካላት ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ወ/ሮ ሊዲያ በመግለጫቸው በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ ከ200 ሜትር ራዲየስ በታች የቤትንግ ስፖርት ውርርድ ማጫወት፣ በማጫወቻ ቦታዎች ጫት፣ ሺሻ እና አልኮል እንዲሁም ተመሳሳይ ነገሮችን ማስጠቀም፤ ያለህጋዊ ፈቃድ ስፖርታዊ ውርርዱን ማካሄድ ፤ በስፍራው የሚደረጉ የእርስ በርስ ግጭቶች ፤ የቡድን ፀብ፤ ከ21 ዓመት በታች የሆኑ ተማሪዎችና ታዳጊዎችን ማወራረድን ጨምሮ የቤቲንግ ቤቶቹ የተላለፏቸው ህጎች መሆናቸውን ጠቁመው ይህም ከህብረተሰቡ ከደረሰ ጥቆማ በተጨማሪ ቢሮው ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በቂ ጥናት አድርጓል ህዝቡንም አወያይቷል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የቤቲንግ ስስፖርት ውርርድ የሚካሄድባቸው ስፍራዎች ልዩ ልዩ ወንጀሎች የሚፈጸሙባቸው ዋነኛ ማዕከላት እየሆኑ መምጣታቸውን ጨምሮ በህብረተሰቡ ላይ እየፈጠሩ ያሉትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዝርዝር ከሚመለከታቸው የፀጥታ ተቋማት ጋር በጥናት በመለየት የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ወ/ሮ ሊዲያ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ከላይ የተዘረዘሩ የህግና ደንብ መተላለፎችን በተደጋጋሚ ሲፈጽሙ የተደረሰባቸው 3ሺህ 241 የቤቲንግ እስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች ላይ መሉ ለሙሉ የማሸግ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊዋ፣ በቀጣይም ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጽሙ ድርጅቶች ላይ ከህብረተሰቡ የሚደርሰንን ጥቆማ ዋቢ በማድረግና በቂ ጥናት በማካሄድ የህግ ማስከበር ስራችንን አጠናክረን እናስቀጥላለን ብለዋል።

የህግ ማስከበር እርምጃው ቀዳሚ ዓላማ ከ21 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ወጣቶችን ከልዩ ልዩ የጥፋት ተግባራት መከላከል፣ የመማር ማስተማር ስራን ከአዋኪ ተግባራት የፀዳ ማድረግና ተዛማጅ የወንጀል ስርጭቶችን በዘላቂነት በመግታት የህብረተሰቡን ማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ሰላም ማረጋገጥ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ገልፀዋል።

ለተጨማሪ መረጃ፦

👉 YouTube https://www.youtube.com/channel/UCagI4q5d_EtvTsajRXWnFjA

👉 Tik Tok https://vm.tiktok.com/ZM6jGNeFE/

👉 Telegram https://t.me/AAcommu

👉 Facebook https://www.facebook.com

👉 Website https://cityaddisababa.gov.et/

Share this Post