ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የሚደረጉ ዉይይቶች የዘመነ የንግድ ስርዓት እና በላቀ ሁኔታ ገቢን ለመሰብሰብ ያግዛል ተባለ፤

-------------

በመዲናዋ ከከተማ እስከ ወረዳ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር እየተደረጉ ያሉ ውይይቶችን አስመልክቶ የከተማ አስተዳደሩ የሁለቱ ቢሮዎች የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ውይይቶቹ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ፤ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለማስቻል ፤ በጋራ መፍትሔ ለመስጠትና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን ማሰባሰብን ዓላማ ያደረጉ መሆናቸውን ሁለቱም ቢሮዎች በጋራ መግለጫቸው ወቅት አመላክተዋል።

በነገው ዕለትም በከተማ ደረጃ የውይይት መርሃ-ግብሩ ቀጥሎ የሚካሄድ መሆኑ በመግለጫው የተጠቆመ ሲሆን በመድረኩም ከደረጃ "ሀ" ፣ "ለ" እና "ሐ" ግብር ከፋዮች የተወከሉ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በጋራ መግለጫው ወቅት እንደተናገሩት፣ በከተማ ደረጃ 210 ሺህ ህጋዊ ንግድ ፈቃድ አውጥተው የሚሰሩ ነጋዴዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ከለውጡ በኋላ የንግዱን ስርዓት በዘላቂነት ለማሻሻል በተሰሩ አካታች ሥራዎች 4መቶ 75ሺህ በላይ ነጋዴዎች ፍቃድ አውጥተው በስራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

አቶ ቢኒያም አክለውም፣ ቢሮው እያከናወነ ባለው ዲጂታል የንግድ አሰራር ስርዓት፣ የምድብ "ሐ" ግብር ከፋዮች በድጂታል አገልግሎት ብቻ ግብራቸውን እንዲከፍሉ መደረጉን ያመላከቱ ሲሆን ከተማ አስተዳደሩ በፍጆታ እቃዎች ፍላጎትና አቅርቦት መካከል የሚስተዋለውን አለመጣጣምና የንግድ ሰንሰለቱን በማሳጠር ምርት በቀጥታ ወደ ሸማቹ የህብረተሰብ ክፍል እንዲደርስ ለማስቻል በከተማዋ አራቱም በሮች ከ6.3 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ ደረጃቸውን የጠበቁ የገበያ ማዕከላት ወደ ንግድ ስርዓቱ እንዲገቡ ተደርጓልም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ በበኩላቸው አጠቃላይ የከተማዋ ገቢ ማደጉን ጠቁመው፣ ከለውጡ በፊት 33 ቢሊዮን ብር የነበረውን የከተማዋን ገቢ ከለውጡ በኋላ በተሰሩ አካታች መዋቅራዊ ለውጦች ምክኒያት በዘንድሮው ዓመት 140 ቢሊየን ብር ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ አደም አክለውም ከተማችን ከምትሰበስበው ገቢ 60 በመቶ ያክሉን ለትምህርት ፣ ለሆስፒታል ፣ መንገድ እና ሌሎች የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ የካፒታልና የዘላቂ ልማት ስራዎች እያዋለች መሆኑን አስረድተዋል።

Share this Post