በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ በበጎፍቃደኞች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመርቀው ለክ/ከተማው ተላለፉ፤

----------

በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ብዙአየሁ ታደሰ ፋውንዴሽን በተሰኘ ድርጅት የተገነቡ 12 መኖሪያ ቤቶች በዛሬው እለት ለክፍለ ከተማ አስተዳደሩ ተላልፈዋል፡፡ 

ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በርክክብ መርሃ-ግብሩ ላይ እንዳሉቶ፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሰፊ የቤት ችግር ካለባቸው ክ/ከተሞች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት በትኩረት በመስራት ላይ ነው ብለዋል። 

ለዘመናት የተከማቸው የመዲናችን የቤት አቅርቦት ችግር በአንድ ጀንበር የማይቀረፍ በመሆኑን የጠቀሱት አቶ ጃንጥራር፣ ደጋግ ባለሃብቶችን በማስተባበር ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፣ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለተወጣው ብዙአየሁ ታደሰ ፋውንዴሽን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው ለሰው ልጅ መኖር መሰረታዊ ጉዳዮች ከሆኑት መካከል ቤት ወሳኝ መሆኑን በመናገር በከተማ አስተዳደሩ የሚስተዋለውን የቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ መንግስት በተለያዩ አማራጮች በመስራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ 

ክፍለ ከተማው የነዋሪዎቹን ችግር ለመቅረፍ የመንግስትና የህዝበን አቅም በማስተባበር ከተሰሩት ስራዎች መካከል 947 የአቅመ-ደካሞች ቤት እድሳት እና በ4 ጣቢያዎች ከ100 በላይ ቤቶችን በመገንባት ለነዋሪዎች ማስተላፍ እንደሚገኝበት የገለፁት የክ/ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አይዳ አወል ገልፀዋል።

ብዙአየሁ ታደሰ ፋውንዴሽን በመጀመሪያው ዙር ለመስራት ቃል ከገባው የ12 አባ ወራ ቤቶች ግንባታ ባሻገር በቀጣይ 18 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደር የ2ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ወለል ግንባታን ለማከናወን ከክፍለ ከተማ አስተዳደሩ ጋር ውል ተፈራርሟል፡፡

Share this Post