04
Jan
2024
------------
በአዲስ አበባ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ከጎበኟቸው ፕሮጀክቶች መካከል በለሚ ኩራ ክ/ከተማ በ60/90 ቀናት የግል ባለሀብቶችንና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተሰሩ ሰፋፊ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች እና አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማዕከል ይገኙበታል።
የለሚ ኩራ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የክ/ከተማውን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠራቸው በጉብኝቱ ላይ ተገልጿል።
አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት፣ የገበያ ሰንሰለቶችን በማሳጠር የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ከተገነቡ ግዙፍ የግብርና ምርቶች የግብይት ማዕከላት አንዱ የሆነውን የለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከልም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጎብኝተውታል።
ለበርካታ እናቶች ዘላቂ የገቢ ምንጭ የሆነውና ለግለሰቦች እና ለተቋማት ጥራቱን የጠበቀ እንጀራ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ የሚገኘው ለሚ እንጀራ ፋብሪካ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶች፣ የተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከላት እና ሌሎችም ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቾች የጉብኝቱ አካል ናቸው።