---------------
የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች እጥረት እንዳይኖር ከተለያዩ ክልሎች ምርት በስፋት ወደ ከተማ እንዲገባ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ እና ህብረት ስራ ኮሚሽን ለመገናኛ ብዙሃን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ እንደተናገሩት መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በከተማችን በቂ ምርተ አቅርቦት እንዲኖር እና ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል በምክትል ከንቲባ ደረጃ የሚመራ ዐብይ ኮሚቴ ተደራጅቶ ላለፉት 15 ቀናት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።
አቶ መስፍን አክለውም የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት ህበረተሰቡ የሚፈልጋቸውን የበዓል ግበአቶች በአቅራቢያው ማግኘት እንዲችልም በከተማዋ ከሚገኙ 179 የእሁድ ገበያዎች መካከል 145ቱ ከሰኞ እስከ ሰኞ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እነዲሁም በከተማዋ በተመረጡ 5 አደባባዮችና ሁለት የገበያ ማዕከላት ባዛሮች እንዲዘጋጁ መደረጉም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ እንደገለጹት ከክልሎችና ከኢንዱስትሪ ምርት አቅራቢ ድርጅቶችጋር ትስስር በመፍጠር ለበዓል የመሰረታዊ ምርቶች በስፋት ወደ ከተማ እንዲገባ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል የጤፍ እና የስንዴ ዱቄትን ጨምሮ ምርቶችን ተቀብለው ለተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን የሚቀርቡ ምርቶች በየአካባቢው አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙ 800 የችርቻሮ መሸጫ ሱቆች እና ከ175 በላይ በሆኑ የቅዳሜና የእሁድ ገበያ ማዕከላትና ባዛሮች በኩል ለተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍል በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡
በተጫማሪም የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን ከአዲስ አበባ የእንስሳት የልህቀት ማዕከል ፤ ከኤልፎራና ከኦሮሚያ ክልል ለሸማቹ ማህበረሰብ በሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች እና በ246 የልኳንዳ ቤቶች በኩል በስፋት የማቅረብ ዝግጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ወ/ሮ ልዕልቲ ተናግረዋል።