ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል 41 በከተማ አስተዳደሩ በጀት የተገነቡ የ2015 የበጀት ዓመት የካፒታል ፕሮጀክቶች ሲሆኑ 24ቱ ደግሞ በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ናቸው።
ፕሮጀክቶቹን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የስራ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በ2015 የበጀት አመት የከተማ አስተዳደሩ 60 በመቶ የሚሆነውን የከተማዋን በጀት ለካፒታል ፕሮጀክቶች በመመደብ እና የከተማውን ህዝብና ባለሀብት በማስተባበር ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ ለህዝብ ተጠቃሚነት እያዋለ ነው ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት የሰጣቸው የትምህርት ፣ የጤና ተቋማት፣ የመንገድ እና የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በከፍተኛ ርብርብ እየተሰሩ መሆናቸውን አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል።
የተገነቡ ፕሮጀክቶች በዘላቂነት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲያደርግም አቶ ጃንጥራር ጥሪ አቅርበዋል።
በፕሮጀክት ግንባታው ሂደት ከ1ሺ 900 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፣ በህዝብ ተሳትፎ ለተሰሩ ፕሮጀክቶች ከ500 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን እና ለካፒታል ፕሮጀክቶችም እንዲሁ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተመድቦ ፕሮጀክቶቹ መገንባታቸውን የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አለምጸሀይ ሽፈራው ተናግረዋል።
ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል የጤና ጣቢያዎች ማስፋፊያ ፣ ትምህርት ቤቶች ፣ የፖሊስ ጣቢያዎች ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች ፣ የወረዳ ማዕከላትን ለስራ ምቹ እና ውብ የማድረግ ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች ፣ የህጻናት እና ወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ይገኙባቸዋል።