ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት በለሚ ኩራ ክ/ከተማ የቅዱስ ጊዩርጊስ የስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ማህበር የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረውን የስፖርት ማዘውተርያ 10 ሺህ ካ.ሜ ቦታ ርክክብ አድርገዋል፡፡

እንደሚታወቀው ከንቲባ / አዳነች አቤቤ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ጋር ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ደጋፊዎቹ ካነሷቸው በርካታ ጥያቄዎች መሀከል አንደኛው የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን የማስፋፋት ጥያቄ ነው፡፡

እነሆ በዛሬው እለት ከንቲባ / አዳነች አቤቤ የወጣቶቹ ጥያቄ አንዱ የሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ማህበር የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ በቦታው ላይ የነበሩ የተለያዩ ህገወጥ ደላሎችንና የይገባኛል ጥያቄዎችን በመፍታት ለክለቡ ደጋፊዎች ማህበር በቦታው በመገኘት አስረክበዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች እንደተናገሩት ይህንን የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ቦታ ብቻ ሳይሆን ሀገርንም የምንገነባው ተባብረን ነው ያሉ ሲሆን ልክ እንደዚሁ ቦታ ሁሉ በከተማው የተለያዩ የልማት ስራዎቻችን ከህገወጥ ደላሎች ጋር ትንቅንቅ በማድረግ የልማት እቅፋቶችን እየተጋፈጥን ነው ስራዎችን እየሰራን ያለነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በየአካባቢው ለልማት እንቅፋት የሚሆኑ ህገወጥ እቅስቃሴዎችን በመግታት ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዛሬ ርክክብ የተደረገበትም ቦታም በፍጥነት ወደ ልማት እንዲገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል የክለቡም ቦርድ በፍጥነት ግንባታውን እንደሚያስጀምር ቃል ገብቷል።

Share this Post