ከመፅሃፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለትውልድ የሚሆኑ 12 የህፃናትና ወጣቶች መጫወቻ እና ስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ግንባታ የማስጀመር ሥራ በዛሬው እለት ተከናውኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፥ በቦሌ እና በየካ ክፍለ ከተሞች በመገኘት የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ሥራውን በይፉ ያስጀመሩ ሲሆን ሌሎች የከተማዋ የሥራ ሃላፊዎችም በ8ቱ ክፍል ከተሞች የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የማዕከላቱን ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከመደመር ትመልድ መፅሃፍ ሽያጭ ገቢ በከተማችን ለህጻናትና ለወጣቶች መዋያ ስፍራ እንድንገነባ በሰጡን እድል ለትውልድ ግንባታ የሚውሉ ማዕከላት ግንባታ አስጀምረናል ብለዋል።
ከተማችን የህጻናትን ሁለንተናዊ መብትና ጥቅም የምታስጠብቅ አፍሪካዊት ብርቅዬ ከተማ እንድትሆን እንሰራለንም ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል::
ከትላንሉ ትውልድ የወረስናቸው ብዙ መልካም ነገሮች እንዳሉ ሁሉ መታረም የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን የገለፀት ከንቲባ አዳነች፥ በሁሉም ረገድ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክት ትውልድን አንጸን ማሳደግ የሁላችንም የቤት ስራ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች ከመጽሐፉ ሺያጭ የሚገኘው ገቢ ለህጻናትና ወጣቶች እስፖርት ማዘውተሪያና መዋያ ስፍራ ግንባታ የሚውል በመሆኑ የከተማችን ነዋሪዎች መጽሐፉን በመግዛት በትውልድ ግንባታ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በግንባታ ማስጀመሪያ መረሀ-ግብሩ ላይ M D W ትሬዲንግ 1.5ሚሊዮን ብር፥ አቶ ብርሃን መሐመድ 1ሚሊዮን ብር፥ ሆራ ትሬዲንግ አምስት መቶ ሺ ብር ፥ የጃፓን ኤምባሲ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ሦስት መቶ መጽሐፍት ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቦሌ አጥቢያ የ200ሺ ብር ግዥ ፈጽመዋል።