የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ባለፉት 12 አመታት ከ4.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸዉን የአዲስ አበባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
ከ2003 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ለግድቡ 1.1 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከ2011 እስከ 2015 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ከ3.2 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምስክር ነጋሽ ገልፀዋል፡፡
12ኛ አመቱ ላይ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ2015ዓ.ም ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ 685 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከያዝነው መጋቢት ወር ድረስ ብቻ 427 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንም ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሃገር ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የተገለፀ ሲሆን ሰፊው ድጋፍ የሚጠበቀው ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ በመሆኑ ግንባታው ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ በ11 ዱም ክፍለ ከተማ ሰፊ የንቅናቄ መድረክ በማድረግ ገቢ የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ደረጃ አሁን ላይ 90 በመቶ መድረሱም ተገልጿል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች እና ባለድርሻ አካላት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ቀርቧል፡፡