የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በነገው እለት 25,491 ቤቶችን ለተጠቃሚዎች በዕጣ ሊያስተላለፍ ነው ፡፡

 

ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የከተማ አስተዳደሩ ከ2006/07 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታቸው ሲካሄዱ የቆዩ በ40/60 ለ3ኛ ጊዜ እና በ20/80 14ኛ ጊዜ በድምሩ 25,491 ቤቶችን ለተጠቃሚዎች በዕጣ ለማስተላለፍ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

👉 በመግለጫው ላይ ከተማ አስተዳደሩ የተረከባቸውን 139 ሺህ ስምንት ቤቶች ውስጥ 96ሺህ ያህል ቤቶች በእጣ ፤በውሳኔ እና በምደባ የተሰጡ መሆኑን ገልፀው በአሁኑ እጣ 25ሺ 491 ቤቶች እጣ እንደሚወጣባቸው አስታውቀዋል፡፡

👉 በተለያየ መንገድ ከተላለፉትም 96ሺህ ቤቶች ውስጥ 54ሺህ ያህሉ ቁልፍ መረከባቸው የተገለፀ ሲሆን ሌሎችም ቁልፍ ያልወሰዱ ቁልፋቸውን እንዲረከቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

👉 በ14ኛው ዙር እጣ ብቁ የሚሆኑትን ተመዝጋቢዎች በተመለከተ የ20/80 ነባር ተመዝጋቢዎች (1997) እስከ የካቲት 21 2014 ዓ.ም ድረስ የቆጠቡና እና የ40/60 40% እና ከዚያ በላይ ቁጠባ ያላቸው እስከ የካቲት 21 2014 ዓ.ም እንደሚሆኑ ተገልጧል፡፡

👉 በዚህም መሰረት በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27,195 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52,599 በአጠቃላይ 79,794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዚህ ዙር ዕጣ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

👉 በዚህ ዙር ከሚተላለፉ ቤቶች ውስጥ ከዚህ በፊት በማጣራት ሂደት የተገኙ ቤቶች ለልማት ተነሺ ሲስተናገዱበት ቆይተው የቀሩት እንዲካተቱ መደረጉን ከንቲባ አዳነች ገልፀዋል፡፡

👉 ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ባለፉት የቤት ልማት ፕሮግራም ከጀመረበት አንስቶ በ17 ዓመታት ውስጥ ለህብረተሰቡ ማቅረብ የተቻለው 300 ሺህ ያህል ቤቶችን ብቻ መሆኑን ገልፀው ፤አሁንም በሚወጡት ውስን ቁጥር ያላቸው ቤቶች የህብረተሰቡን ችግር መቅረፍ ስለማይችሉ ፤ከተማ አስተዳደሩ አምስት አይነት የቤት ልማት አማራጮችን መዘርጋቱን አስታውቀዋል፡፡

👉 ከነዚህም መሃከል

➡️ በመኖርያ ህብረት ስራ ማህበር ፤12ሺህ ያህል ሰዎች ከነበሩት ተመዝጋቢዎች ውስጥ አሁን ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

➡️ በመንግስትና በግል ባለሀብቶች አጋርነት /public private partnership/ በ70/30 የግንኙነት ስርዓት

➡️ በመኖርያ ቤት በሽርክና ማቅረብ/Joint Venture /፣

➡️ የግል አልሚዎች በማበረታታት የህብረተሰቡን የቤት ችግር ለመፍታት አስተዳደሩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

➡️ የቁጠባ ቤቶችን መገንባት በተመጣጣኝ ኪራይ ማቅረብም አማራጭ

👉 እንደ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አገላለፅ ‹‹ይህ አመራር የተረከባቸው ቤቶች በአጠቃላይ በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩባቸው ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ ፤የማስተላለፍያ፤ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር ፤ የቤቶቹን ግንባታ ጥለው የጠፉ ኮንትራክተሮች ፤ የብድር አቅርቦት እግር እንዲሁም የዋጋ ንረት የመሳሰሉት ተግዳሮቶችን መጋፈጡን አስታውሰዋል፡፡

👉 ነገር ግን እነዚህ እክሎች በማለፍ በአጠቃላይ አስተዳደሩ ከባንክ ቦንድ ብድር ብር 18.7 ቢሊዮን እና ለመሠረተ ልማት ግንባታ ከመደበኛ በጀት ብር 2.871 ቢሊዮን በድምሩ ብር 21.571 ቢሊዮን መቻሉን ገልፀዋል፡፡

👉 የአንድ ካሬ ማስተላለፊያ ዋጋን በተመለከተም 20/80 ቤት ልማት ፕሮግራም 7,997.17 ብር 40/60 ቤት ልማት ፕሮግራም 11,162.97 ብር ሲሆን በግል አልሚዎች ከሚሰሩ ተመሳሳይ ቤቶች አኳያ ይህ የአንድ ካሬ ማስተላፊያ ዋጋ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ቀርቧል፡፡

👉 የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘር ያስሚን ዋህብረቢ በበኩላቸው ቤቶቹ 97 በመቶ አማካኝ አፈፃፀም ላይ የደረሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

👉 አሁን የምንጠቀምበት የእጣ አወጣጥ ሶፍትዌር በተመለከተ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ) ያበለፀገውና ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የፌደራልንም ጨምሮ ታይቶ ይሁንታን ያገኘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

👉 በመበልጸግ ሂደት ብዙ ሙከራዎች የተካደለት ቅድመ-ዝግጅት ለአራት ዙር ሙከራ ተደርጎበት፣ አምስተኛውና የመጨረሻ ዙር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከታዛቢዎች ተገኝቶ እንደሚሞከር ተገልፅዋል፡፡

👉 ሲስተሙ ተጠያቂነትን ማስፈን የሚችል ኦዲት መደረግ የሚችል መሆኑ ገልፀዋል፡፡

👉 አቶ ሽመልስ ታምራት የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የቤት አወጣጡ እንደ ቅደም ተከተል ቅድሚያ የ97 ተመዝጋቢዎች እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡

👉 ለዕጣ የቀረቡ ቤቶች የሚገኙባቸው ሳይቶች፣ የቤት ዓይነትና ብዛት በተመለከተ

➡️ የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም

አያት 2፤ ቦሌ በሻሌ፤ ቡልቡላ ሎት 2 ሲሆኑ

➡️ የ20/80 ቤት ልማት ፕሮግራም

በረከት፤ቦሌ አራብሳ (ሳይት 3፤5፤6)፤ ወታደር፤የካ ጣፎ፤ ጀሞ ጋራ፤ ጎሮ ስላሴ፤ፉሪ ሃና እና ፋኑኤል ናቸው፡፡

➡️ በዚህ አጋጣሚ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የተጀመሩት የተገጣጣሚ ቤቶች የነበረባቸው የፍርድ ቤት እግድ ተነስቶ በፍጥነት እየተገነባ መሆኑ ተገልጧል፡፡

 

 

 

 

 

Share this Post