በለሚ ኩራ ክ/ከተማ በከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስተባባሪነት ባለፉት ጊዜያት ሲከናወኑ የቆዩ የ60/90 ቀናት ሰው ተኮር ስራዎችን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የተለያዩ የሚድያ አካላትን አስጎብኝቷል፡፡
አመራሩ በከፍተኛ ቁርጠኝነት በ60/90 ቀናት የሚተገበሩ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን ህብረተሰቡንና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቀናዒ የሆኑ የግሉን ሴክተር በማስተባበር እያከናወኑ እንደሚገኙ በጉብኝቱ መክፈቻ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዶኒያስ ወ/አረጋይ ተናግረዋል
ባለፈው አመት የተጀመረውና ተሞክሮ ተወስዶ ዘንድሮም ተጠናክሮ የቀጠለው በተለያዩ ክፍለ ከተሞች አጠቃላይ በመልካም አስተዳደርን ጨምሮ የህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች በተደራጀ መንገድ እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው ከፊታችን ባሉ ቅርብ ቀናት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ይበቃሉ ብለዋል።
በክፍለ ከተማው የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ለማደናቀፍ በመጠናቀቅ ላይ ወደሚገኘው አዲሱ ህንጻ ሰነዶች የተዘዋወሩ መስሏቸው አጥፊዎች ህንጻውን በእሳት የማቃጠል ሙከራ ቢያደርጉም አስተዳደሩ እንደገና ህንጻው ከበፊቱ የበለጠ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ እያደረገ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ በላይ ታደለ የለሚኩራ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡
የሰው ተኮር ዕቅዶችን በፍጥነት መሬት ማውረድ እንዲቻልና ለዜጎች በቅርበት አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ምቹ የኑሮ አካባቢን ለመፍጠር ኢላማ በማድረግ በክፍለ ከተማው የሚከናወኑ የልማት ተግባራት በክላስተር ተከፋፍለው እንዲተገበሩ እየተደረገ ይገኛልም ሲሉ ገልፀዋል።
ለሁለት ሺ አራት መቶ እናቶች አገልግሎት የሚሰጥ የእንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግም አቶ በላይ ጠቅሰዋል፡፡
አንድ ሺ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎች መመገብ የሚቸል ማዕከል በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግ በንግግራቸው የጠቀሱ ሲሆን ከሰላሳ ለሚበልጡ እናቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ጨምረው ገልጠዋል ።
የመሬት ፣የወሳኝ ኩነትና የቤቶች አገልግሎትን የመሳሰሉ ተግባራትን በአጠቃላይ በቴክኖሎጂ ለመስጠት የሚያስችል አሰራር በሚቀጥሉት ቅርብ ቀናት በክፍለ ከተማው ይፋ ይደረጋል ተብሏል ።