02
Aug
2021
ከ165 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት በህገ ወጥ መንገድ ሲመዘዋወሩ የነበረ የኮትሮባንድ እና በተለያዩ መጋዘኖች ተከማችቶ የተገኙ ልዩ ልዩ ምርቶች መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቢሮው የ2013 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም የቢሮው ከፍተኛ አመራሮች እና ከክፍለ ከተማ ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊዎችን ጋር በዝርዝር ገምግሟል። በበጀት ዓመቱም 165 ሚሊዮን 016 ሺህ,389 ብር የሚገመት በህገ ወጥ መንገድ ሲመዘዋወሩ እና በተለያዩ መጋዘኖች ተከማችተው የተገኙ ልዩ ልዩ ምርቶችን በመውረስ ለመንግስት ገቢ መደረጉን የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ገልጸዋል፡፡ በንግድ ቁጥጥር ስራ ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ 325 ሺህ የንግድ ድርጅቶች የንግድ ህግን ተከትለው እየሠሩ መሆናቸውን ለመከታተልና ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ከህግ ወጪ ሲሰሩ የተገኙ 54 ንግድ ድርጅቶች ላይ የንግድ ፈቃድ እስከ የማገድ ድረስ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተሳሳተ እና ልኬት በታች ሲለካባቸው የነበሩ 1ሺህ 459 የልኬት መሳሪያዎች እና ሚዛኖች በቁጥጥር ስር ውለው እንዲወገዱ ተደርጓል ብለዋል ። በ2013 በተለያዩ ንግድ መስኮች ለሚሠማሩ 112ሺህ 941 አዳዲስ ነጋዴዎች ንግድ ፈቃድ እንደተሰጠ አቶ አብዱልፈታ ጠቁመዋል፡፡ በ2014 በጀት ዓመትም የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን የሚያስችሉ የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር አቅጣጫ ተቀምጧል።