የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት በከተማዋ በግንባታ ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ። የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ዘርፈሽዋል ንጉሴ፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እና አ...

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት በከተማዋ በግንባታ ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ። የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ዘርፈሽዋል ንጉሴ፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እና አባላት በጋራ በመሆን የአድዋን ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቢሮ የእድሳትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ዘርፈሽዋል ንጉሴ በጉብኝቱ እንደገለጹት በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙት ሜጋ ፕሮጀክቶች ታሪክን በሚዘክር መልኩ በተቀመጠላቸው ጊዜ ግንባታቸው እየተከናወነ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እና የቢሮ ህንፃ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለፁት አፈ ጉባኤዋ ሁሉም ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እና ጥራት እንዲጠናቀቁ ምክር ቤታቸው የክትትልና ቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ለምክር ቤቱ አባላት ስለፕሮጀክቶቹ ማብራሪያ የሰጡት ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ጽ/ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር መሬሳ ልክሳ፤ ለአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት ህንፃ ግንባታ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተበጅቶለት እየተከናወነ ሲሆን በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆኖል ብለዋል። ፕሮጀክቱ የአድዋ ታሪክ በሚዘክር መልኩ የምክር ቤት ቢሮ፣በአንድ ጊዜ 4 ሽህ ሰዎች ማስተናገድ የሚችል የምክር ቤት አዳራሽ፣ 11 ሺህ መኪናዎችን ማስተናገድ የሚችል የመኪና ማቆሚያ፣ ዘመናዊ ላይቤሪያ እና የምርምር ማዕከል እንዳለውም ተናግረዋል። በተመሳሳይ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቢሮ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በዘመነ እና ለስራ ምቹ በሆነ መልኩ የህንፃ እድሳቱ እየተከናወነ መሆኑን ኢንጅነር መሬሳ ተናግረዋል። ለህንፃው እድሳት 62 ሚሊዮን ዶላር የተመደበለት ሲሆን አጠቃላይ የህንፃው እድሳት ክንውን አሁን ላይ 80 በመቶ መድረሱንም ምክትል ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል።

Share this Post