የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች አስተዳደሩ ለብዝሀ ቋንቋ አተገባበር ከአፍ መፍቻ በተጨማሪ የሀገር ውስጥና የውጪ ቋንቋዎችን በስርዓተ ትምህርት ለማካተት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ ባደረገው የጥናት ውጤት ላይ ውይይት ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጥናቱ ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በውይይት እየዳበረ መሆኑን አስረድተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችም በግልፀኝነት ተወያይተውበት በቀጣይ ህዝቡን ማወያየት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል::
የጥናት ፅሁፉን ያቀረቡት የኮተቤ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶ/ር ዮሴፍ ከአንድ በላይ ቋንቋዎችን ማወቅ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ማህበራዊ መስተጋብርንና ትስስርን የማጠናከር እና ሌሎች ፍልስፍናዊና ባህላዊ እውቀቶችን እንደሚያጎናፅፍ፤ በአገራችንም በተለይም በኦሮሚያ በአማራ በሶማሌ በደቡብ ክልል እና ከሌሎች ክልሎች ጋር በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎችና በሌሎችም ክልሎች የተጀማመሩ ስራዎች ያስገኟቸውን መልካም ውጤቶች በመጥቀስ አብራርተዋል።
በተደረገው ጥናት ከአገር ውስጥ ቋንቋዎችና ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ከቅርበት ከተደራሽነት እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምክንያቶች ሌሎች የአካባቢው ቋንቋዎችንም ለመማር ምርጫቸው መሆኑ በጥናቱ መረጋገጡ ቀርቧል።
ጥናቱ የተማሪዎችን፣ የመምህራንንና የወላጆችን ሀሳብ ያካተተ ለምሁራን ቀርቦ በተጨማሪ ግብዓት የዳበረና በቀጣይም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም በውይይታቸው የበለጠ የሚያዳብሩት መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ የተሳተፉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮችም ለብዝሀ ቋንቋ አተገባበር ከአፍ መፍቻ በተጨማሪ የሀገር ውስጥና የውጪ ቋንቋዎችን መማር የጥናት ውጤትም መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያረጋገጠ መሆኑንና የቀጣዩ ትውልድ ማህበራዊ ትስስር የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብዝሀ ቋንቋ አተገባበር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል።