የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀምና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎችን ግምገማ አካሄደ።

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት 9 ወራት በከተማው የነበረውን አፈፃፀም ከከተማው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋራ ገመገመ ሲሆን፥ በማጠቃለያውም የቀጣይ የርብርብ ማእከል የሆኑ አቅጣጫዎችም ተቀምጧል፡፡

በጥንካሬ የተነሱ ዋና ዋናዎቹ ከሰላም አኳያ የተሰሩ መልካም እና አበረታች ስራዎች፤ ከፕሮጀክት አፈፃፀም አንፃር የታዩ ጠንካራ ጎኖች፤ በውሃ እና በመንገዶች ላይ የታዩ መልካም እንቅስቃሴዎች፤ በዲዛይንና ኮንስትራክሽን፤ በስራ እድል ፈጠራ፤ በገቢና በትምህርት እንዲሁም በጤና ዘርፍ መልካም አፈፃፀም መታየቱ ተገምግሟል፡፡

የኑሮ ውድነቱን ለማርገብም የተደረገው ርብርብ አበረታችን እንደነበርም የተቀመጠ ሲሆን በተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችም በርካታ ጠንካራ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸው ነው የተገለጸው፡፡

የከተማ አስተዳደሩም በህልውና ዘመቻው የደጀንነት ሚናውን በመወጣት ከፍተኛውን ድርሻ ወስዶ ውጤታማ ሥራ ማከናወኑንም ተገልጿል፡፡

በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችም የአገልግሎት አሰጣጡን በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ርብርብ የሚደረግበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ስራ እንዲሁም ሌብነትና ስርዓት አልበኝነትን ማስተካከል ትኩረት የሚሰጠው እና ህዝቡን በማሳተፍ የሚከናወን መሆኑን ነው የተገለጸው፡፡

የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት የሚሻ መሆኑ የተነሳ ሲሆን የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅና አማራጭ የቤት አቅርቦት ሞዳሊቲን ማስፋትና የመፈፀም አቅም መገንባትም በትኩረት የሚሰሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ህብረተሰቡን በየደረጃው በተለያዩ አጀንዳዎች ማወያየት እና ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዲሁም የተጀመረው የከተማ ግብርና ስራን አጠናክሮ መቀጠል እና 4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ስራን ከተቋማት ጀምሮ በተደራጀ መንገድ መፈፀም የቀጣይ ጊዜያት አቅጣጫ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ እንደገለጹት፡- በርካታ ውጤታማ ስራዎች ባለፉት 9 ወራት ማከናወን ተችሏል ያሉ ሲሆን በተለይ ህዝቡን የፀጥታ ስራ ባለቤት በማድረግ ጠንካራ ስራ ተሰርቷል፡፡

ከንቲባዋ እንደገለጹት፡- በሌሎችም ዘርፎች የታዩ መልካም ውጤቶች ይበልጥ ተጠናክረው፤ ጉድለቶች ታርመው እንዲቀጥሉ ችግር ፈቺ አመራር መሆን አለብን፡፡

ተቋማትን መገንባትና ተቋማዊ ቅንጅት ብሎም ስርዓት መገንባት አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ መልካም ልምዶችን ማስፋትም በሁሉም አመራሮችና በሁሉም ተቋማት የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት ተመላክቷል፡፡

Share this Post