ከንቲባ አዳነች አቤቤ
የጥምቀት በዓል በማይዳሰስ ቅርስነት ከተመዘገቡ ድንቅ የኢትዮጵዊነት ማሳያ ፣ውድ ሃብታችን ፣ ድምቀታችንና የሀገራዊ ኩራት ምንጭ ከሆኑ በዓሎቻችን አንዱ ነው::
ጥምቀት የፍቅር ፣የሰላም ፣ የደስታ ፣የአብሮነት፣ የመተሳሰብ ፣የፀሎትና የበጎነት ወቅት ነው፡፡በጥምቀት በአል ጥላቻ በጥምቀተ ባህሩ በፍቅር ታጥቦ የሚነፃበት ፣ መለያየት በአንድነትና ፍቅር የሚተካበት ፣ ቂም ለይቅርታ እና አብሮነት ቦታውን የሚለቅበት፣ ፀብ በእርቀ ሰላም የሚዘጋበት ፣ አንደበቶች ፍቅርን የሚዘሩበት ፣ የጥላቻ መሰረቶች የሚናዱበትና ሰላምና ደስታ የሚነግስበት ወቅት ነው፡፡በተለይም የዘንድሮ የጥምቀት በአል በሃገራችን ሉአለዊነት ላይ የተቃጣውን ወረራና ጦርነት በአንድነትና በከፍተኛ ኢትዮጵያዊ ወኔ በመከትንበት ማግስት የምናከብረው እንደመሆኑ መጠን አሁንም ይህንን ህብረታችንንና አንድነታችነን አጠናክረን የምንቀጥልበት፤ለልዩነቶች በር የሚከፍቱ እድሎችን የምንዘጋበት፤ የኢትዮጵያን ትንሳኤ በአንድነታችን ላይ የምናፀናበት በዓል ይሁንልን!
ጥምቀት ለከተማችን አዲስ አበባ ልዩ ገፅታን የሚያላብስ የአይን ማረፍያ በአሎቻችን አንዱ በመሆኑ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ፤ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ አስተዋዩ ፣ ጨዋዉና ሰላም ወዳዱ የከተማችን ህዝብ ወትሮም እንደምናደርገው ሁሉ በትብብርና በአብሮነት አካባቢያችንን በንቃት በመጠበቅ ፤ ከፀጥታ ሃይሎቻችን ጋር በትብብር በመስራት ፤ እንደሰናሳልፈው ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ !!
በድጋሚ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!