በመዲናችን አዲስ አበባ የተካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት ተጀምሮ በስኬት ተጠናቋል፡፡
ጉባኤ በአፍሪካዊ ወንድማማችነት እና የአንድነት መንፈስ ተካሂዶ ጠቃሚና አስፈላጊ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡
ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ መላው የከተማችን ነዋሪዎች ፤ላሳያችሁት ፍፁም ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነትና አክባሪነት ልባዊ ምስጋናችንን እና አድናቆታችንን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
ይህ ጉባኤ ለኢትዮጵያችን የተለየ ትርጉም እንዳለው በመረዳት ጥሪያችንን አክብራችሁ አካባቢያችሁን በማፅዳት ፣ ከተማውን በማስዋብ፣ በመብራት በማድመቅ እና በተለያየ አፍሪካዊ እሴቶች በማሸብረቅ ለጉባኤው ድምቀት በልዩ ሃገራዊ ስሜት ሃላፊነታችሁን ስለተወጣችሁ የግልና የመንግስት ተቋማት ሁሉ ልባዊ ምስጋናችን በያላችሁበት ይድረሳችሁ ።
በየደረጃው የምትገኙ የከተማችን አመራሮች፣ የፀጥታ ሃይሎች ፣ ለፕሮግራሙ ስኬት የተባበራችሁና የተሰማራችሁ ተቋማትና ድርጅቶች ይህ ታሪካዊ ጉባኤ በመዲናችን በሰላም ተጀመሮ ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቅ ላሳያችሁት ትጋትና በስነምግባር የተሞላ ኢትዮጵያዊ መስተንግዶና ልትመሰገኑ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በዚህ ጉባኤ ኢትዮጵያዊ ልማዳችን እና ባህላችን ጎልቶ የታየበት ፣ ከተማችን አፍሪካዊ እሴትን ተላብሳ ደምቃና ተውባ የታየችበት ፣ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ያለነን አክብሮትና ፍቅር የገለፅንበት፣ እንደ ሁልጊዜውም ሀገራችን ኢትዮጵያ ለፓንአፍሪካዊ አስተሳሰብ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠችበት በመሆኑ ይህንን ህብረታችን እና አንድነታችንን አጠናክረን በመቀጠል የኢትዮጵያን ትንሳኤ በማረጋገጥ የአፍሪካ ፈርጥ ሆነን እንቀጥል ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!!"
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ