"የተቃጣብንን ዘርፈ ብዙ ጥቃት መመከት የቻልነው በአንድነት ስለተነሳን ነዉ"ከንቲባ አዳነች አቤቤ

 

የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ እና ባለሀብቶች ፤ የጥበብ ባለሙያዎችና ዳያስፖራዎች ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በጦርነቱ ሣቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ከ34ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

"ከኢትዮጵያ የሚበልጥብኝ የለም" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የድጋፍ ፕሮግራም ላይ የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን ሀብቱ የተሰበሰበውን 23ሚሊዮን 242ሺህ 290 ብር የሚገመት ድጋፍ ለአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስረክበዋል ፤ እንዲሁም አንጋፋዋ አርቲስት ሀመልማል አባተ አንድ ሚሊዮን ፤የአሌክሳንድሪያ ሆቴል ባለቤት አቶ ዮሐንስ ደርሶ 5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም አቶ በቀለ አረና የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል ።በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከዉስጥም ከዉጪም ባሉ ሀይሎች የተቃጣብንን ዘርፈ ብዙ ጥቃት መመከት የቻልነው በአንድነት ስለተነሳን ነዉ ፤ በመሆኑም በቀጣይም በአሸባሪዉ ቡድን የወደሙ አካባቢዎችንና ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋምና በራስ አቅም ብልፅግናናልማትን በማረጋገጥ ረገድ ትብብራችንን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ነዉ ያሉት።

በተጨማሪም ክብርት ከንቲባዋ ከተቋሙ ዛሬ ለተሸኙ 47 ዘማች አመራሮችና ሰራተኞች ባስተላለፉት መልእክት "በአሸባሪዉ ቡድን የወደሙ በርካታ አካባቢዎች እና ተቋማት ላይ እየተካሄደ ላለው ፈጣን የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራዎች ላይ በተቋሙ ያዳበራችሁት ሙያዊ ክህሎት እጅጉን ወሳኝ በመሆኑ የበኩላችሁን ሙያዊ እገዛ በማድረግ ደጀንነታችሁን እንድታስመሰክሩ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ ብለዋል።

እስከአሁንም በከተማ ደረጃ በ3ኛዉ ዙር ብቻ ከ3ቢሊዮን ብር በላይ ለአገር መከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ ሀይሎች እንዲሁም በወራሪው ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ማቋቋሚያ የሚዉል ሀብት መሰብሰብ መቻሉን የገለፁት ከንቲባዋ ለዚህም ከትርፋችሁ ሳይሆን ካላችሁ ሳትሰስቱ ለእናት አገር ጥሪ ፈጣን ምላሽ የሰጣችሁ መላው የከተማችን ነዋሪዎች የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል ። ድጋፍ የተሰበሰበው በቢሮዉ ስር ከሚገኙ አመራሮችና ሰራተኞች ፤ የቴክኒክናሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ፣ የአይሲቲ ተቋማት ሲሆን የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች የ#በቃ ወይም #Nomore አለምአቀፍ እንቅስቃሴን በይፋ ተቀላቅለዋል በዚህም ምዕራባዊያን አገራትና ሚዲያዎቻቸው በኢትዮጵያ ዉስጣዊ ጉዳይ ላይ አሉታዊ በሆነ መልኩ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እና የአሸባሪዉ የህወሓት ቡድንን እኩይ ተግባር አዉግዘዋል።

#አካባቢያችንን እንጠብቅ!

#ወደ ግምባር እንዝመት!

#መከላከያን እንደግፍ!

Share this Post