" ከደጀን እስከ ግንባር ለሀገራችን መክፈል የሚገባንን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን" - የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

 

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህልውና ዘመቻ ላይ የጀመሩትን እንቅስቃሴ ለማቀናጀት የሚያስችል የውይይት መድረክ አካሂደዋል ።

አንድ ሆነን የተደቀነብን ፈተና የሚጠይቀው መስዋዕትነት የሀገርና የህዝብ ህልውና የማረጋግጥ ታሪካዊ የትግል ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ያሉት የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ፤ሁላችንም ያለችንን አንድ ሀገር ከወራሪ ጠላት የማዳን የጋራ ሃላፊነት አለብን ብለዋል። በመሆኑም አንድ ላይ ቆመን በመፋለም ታሪካዊ ድል ከማስመዝገብ ውጭ አማራጭ የሌለው ትግል ነው::ለመላው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጠላት የሆነው አሸባሪው የህወሓት ቡድንን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ እና ማህበረሰባዊ እድገት ጠንቅ የሆነው ከእኔ ውጭ ላሳር የሚል ሀሳቡ ጭምር መደምሰስ ነው ያለበት ሲሉ አቶ መለሰ ተናግረዋል ።

ከዚህ አሸባሪ ሃይል ጀርባ ብዙ ተዋናይ መኖራቸውን የገለጹት አቶ መለሰ የእነዚህንም ተዋናይ ያልተገባ አካሄድ በመግራት እውነታችንና ሉዓላዊ ክብራችንን ለማስጠበቅ በጋራ መሰራት እንዳለበት አንስተዋል ።የእኛ አቅም አንድነታችን ነው፤ ይህን አንድነታችንን በጠላት ሃይል ላይ እንዲያርፍ እና የሀገራቸን የግዛት አንድነት አደጋ ውስጥ የሚጥል ነገር እንዳይፈጠር ለአንድ ሀገራችን በጋራ ተሰልፈን አንድነቷን ማጠናከር ይገባናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

ሀገርን ከጠላት መጠበቅ የመንግስት ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን የገለጹት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች የተከፈተብን ጦርነት እንደ ህዝብ ነውና አንድ ላይ በመሆን እንደ ህዝብ ተደራጅተን መመከት ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል ።

ስልጣን በምርጫ እንጂ በጦርነት አይመጣም ያሉት አመራሮቹ ሊያጠፋን የመጣውን አሸባሪ ሃይል አቅማችንንና ሃይላችንን በማሰባሰብ ወደዚህ ሃይል መዝመት አለብን ሲሉ ተናግረዋል ።"ከደጀን እስከ ግንባር" ለሀገራችን መክፈል የሚገባንን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ያሉት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ በመስራት ኢትዮጵያን ለመታደግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል ።በመጨረሻም በከተማ በየአከባቢው እየተደራጀ ባለው የህዝብ ሰራዊት እንዲሁም የጸጥታ ስራዎች ከመንግስትና ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅነት እየሰሩ እንደሆነና ስራቸውንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲ አመራሮች አሳውቀዋል ።

Share this Post