''የኢትዮጵያ እውነት እንደደመራው ሁሉ በብርሃን አንጸባርቆ ይወጣል":-ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

 

በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉትምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የመስቀል በዓል ኢትዮጵያን በዓለም ያስተዋወቃትና የቱሪዝም መስህብ በመሆኑ ትልቅ አስተዋዕኦ እያደረገ ያለ ሀገራዊ ሀብታችን ነው ብለዋል።

በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ መስቀል ጨለማን የገለጠ፥ የብርሃንን አሸናፊነት ያሳየ፤ አዲሰ ተስፋን ያበሰረ ከድንግዝግዝ ጨለማ ውስጥ አስደናቂ የሆነ ብርሃን መገኛ ማሳያ እንደሆነ ምክትል ከንቲዋ አመልክተዋል።

መስቀሉም እየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ሲል ውድ የህይወት ዋጋ የከፈለበት ሆኖ ሳለ፤ክፉዎች መስቀሉንና የመሰቀሉን ግማድ ለመደበቅ የቆሻሻ ክምር በመከመር የመስቀሉን ሃይልና የፈውስ ምንጭነት ለመሰወር ከንቱ ጥረት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል ።

መስቀሉን በቆሻሻ ለመሸፈን እንደሞከሩ ሁሉ የኢትዮጵያን እውነት ለመሸፈን የሚሞክሩ ሃይሎች ጥረት መቼም ቢሆን አይሳካላቸውም ፤ኢትዮጵያን ከከበባት ጠላት ለመጠበቅም የመስቀል ዋጋን ከፍለንም ቢሆን ልንጠብቃት ይገባል ብለዋል።

ይህንን ከሀገራችን አሁናዊ ሁኔታ ጋር በመስተያየትም የመሰቀሉን እውነት በቆሻሻ ክምር ሊጋርዱት እንደጣሩት ክፉዎች ሁሉ፥ የሀገራችንን የኢትዮጵያን እውነት ሊጋርዱ፤ ሊያጠለሹና የውሸት ቆሻሻ ሊከምሩ እየተጉ ያሉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ሙከራቸው ሊሳካ እንደማይችልም ምክትል ከንቲባዋ በአጽንኦት ተናግረዋል ።

የውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያን እኛ ካላስተዳደርን እናፈርሳታለን ብለው ከተነሱት የእናት ጡት ነካሽ ከሆኑ ከሃዲዎች ጎን ቆመው ሊያንበረክኩን ቢሞክሩም ፣ የቆሻሻ ተራራን ንደው ከተቀበረበት ቆፍርው እንዳወጡት ጽኑዓን ሁሉ እኛም ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን ዋጋ እየከፈልን አገራችንን ከከበባት ሀሰት፣ ትዕቢትና ዘርፈ ብዙ ጫና እናላቅቃታለን ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ትላንት ተመክታበት ያልጣላት ዛሬም የምትመካበት ፈጣሪዋ እና በህዝቦችዋ እውነቷ ያበራል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ የኢትዮጵያ እውነት እንደደመራው ሁሉ በብርሃን አንጸባርቆ እንደሚወጣ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል፡፡

Share this Post