ህብረቱ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ተገለጸ ****************************

 

የ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

ለጉባኤው ስኬታማነት ነዋሪዎች፣የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣አመራሮችና የኮቪድ ፕሮቶኮልን በመጠበቅ የጤና ሙያተኞች፣ዘገባዎችን ተደራሽ በማድረግ መገናኛ ብዙሀን ምስጋና ቀርቦላቸዋል።በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ዮናስ ዘውዴ የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለዓለም አሳይቷል ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የከተማ አስተዳደሩ የስድስት ወራት አፈፃፀም ግምገማ የተሻለ ውጤት መገኘቱንና አገልጋይነት የከተማ አስተዳደሩ ቀዳሚ ስራ እንደሚሆንም ሃላፊው ተናግረዋል።የቢሮው ሃላፊ ቻይና በአዲስ አበባ የቻይና ማዕከል ሊገነባ መሆኑንና የማዕከሉ መገንባት የኢትዮጵያ፣የአፍሪካና ቻይናን የባህልና የዲፕሎማሲ ግንኙነትን እንደሚያጠናከር ተናግረዋል።የአፍሪካ የቀርከሃ ሰርቶ ማሳያ የስልጠና ማዕከልም በቻይና የፋይናንስ ድጋፍ በአዲስ አበባ ሊገነባ መሆኑንም የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል።

በጊዜ ባለመልማቱ ከ13 የአፍሪካ አገራት ኤምባሲዎች ተነጥቆ የነበረው መሬት ለየኤምባሲዎቹ እንዲመለስላቸው መወሰኑንም ኃላፊው አስታውቀዋል።

 

 

Share this Post