የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የጠራው ስብሰባ ፖለቲካዊ አላማ የያዘ ነው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የጠራው ልዩ ስብሰባ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያለው ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።የምክር ቤቱ አባላት የተጠራውን ስብሰባ ውድቅ እንዲያደርጉም ጠይቋል።የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ የጠራው ስብሰባ ድርጅቱና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረጉት የጣምራ ምርምራና መንግስት የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እያደረገ ያለውን ጥረት የገፋ መሆኑን አስታውቋል።
በጥምር ሪፖርቱ የቀረቡ ምክር ሀሳቦችን መንግስት ተቀብሎ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውሷል።ይህ ባለበት ሁኔታ በምክር ቤቱ የተጠራው ልዩ ስብሰባ ፍላጎት ፖለቲካዊ አላማ ለማሳካት እንደሆነ በግልጽ መረዳት እንደሚቻል አመልክቷል።አንዳንድ አገራት ምክር ቤቱን ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ አድርገው መጠቀማቸው ኢትዮጵያን እንዳሳዘናት ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ምክር ቤቱን አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈፀማቸውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ላይ ምርምራ ማድረግ ሲጠበቅበት በተወሰኑ አገራት የፖለቲካ ፍላጎት ምክንያት ያን አለማድረጉን አስታውቋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ይህን ያልተገባ አካሄዱን በአስቸኳይ ማቆም እንዳለበት አመልክቷል።
የምክር ቤቱ አባል አገራትም ይህንን የተወሰኑ አገራትን የፖለቲካ አላማ ለማስፈጸም የተጠራውን ልዩ ስብሰባና ውጤቱን በመቃወም ውድቅ እንዲያደርጉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ አሁንም የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና እንዲጠበቁ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ የምክር ቤቱ አባላት ልታረጋግጥ ትወዳለች ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው።
#አካባቢህን ጠብቅ፣
#ወደ ግንባር ዝመት፣
#መከላከያን ደግፍ።