በትላንትናው ዕለት ከሰዓት በኃላ በጣለው ከባድ ዝናብ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 መካኒሳ በሚገኘው መካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ ቅጥር ግቢ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ያስከተለ ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል፡፡
ምክትል ከንቲባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፣በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ጋር በመሆን በጎርፍ አደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች በቦታው በመገኘት አፅናንተዋል።
በትላንትናው ዕለት የደረሰው የጎርፍ አደጋ በከተማዋ እስካሁን ከተከሰቱት የጎርፍ አደጋዎች ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተጎጂዎችን የማቋቋም ፣የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፍ እንዲያገኙ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡በከተማዋ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ እና የውሃ ተፋሰስ ስፍራዎችን የማጽዳት ስራ ለማከናውን እና የጎርፍ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት አመላካች መሆኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበበ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍሰሃ በበኩላቸው ትላንት ከእኩለ ቀን ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ በህይወት እና ንብረት ላይ የደረሱ ጉዳት እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡እስካሁንም በጎርፍ አደጋው የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና አጠቃላይ በህይወት እና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በቀጣይ ይፋ እንደሚደርግ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡