በአዲስ አበባ በአንድ ግለሰብ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ውስጥ ተቀጣጣይ ቁሳቁሶችና ኬሚካሎች መያዛቸውን የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
የአዲስ አበባ ፖሊሰ ኮሚሽን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ተቀጣጣይ ቁሳቁሶችና ኬሚካሎችን ሸቀጣ ሸቀጦችን እንደሽፋን ተጠቅሞ በመደብሩ ውስጥ ደብቆ የተገኘው በአሁኑ ወቅት ነዋሪነቱን በሳውዲ አረቢያ ያደረገ አቶ መሀመድ ሀሰን የተባለ ግለሰብ ነው።ግለሰቡ ከመንግስት ለውጡ በፊት ለሽብርተኛው ህወሃት በርካታ ገንዘብ በመላክ ከቡድኑ አመራሮች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር "ተቀጣጣይ ቁሶችና ኬሚካሎችን ችርቻሮ ንግድ" በሚል ፍቃድ አውጥቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ግለሰቡ ይሄንን የንግድ ፈቃድ ከመንግስትለውጡ በኋላ "የሸቀጣ ሸቀጥ ችርቻሮ ንግድ" በሚል ቀይሮ ሲንቀሳቀስ የቆየ መሆኑን አመልክቷል፡፡
የደህንነትና ፀጥታ አካላት ጉዳዩን በጋር ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ የግለሰቡ የሸቀጣ ሸቀጥ ችርቻሮ ንግድ መደብር በሚገኝበት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ቀጣና 5 አካባቢ በተደረገ ፍተሻ በርካታ ተቀጣጣይ ቁሳቁሶችና ኬሚካሎችን መገኘታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በተያያዘ በአንድ ግለሰብ ባንክ ደብተር ውስጥ ከነበረ 40 ሚሊዮን ብር 13 ሚሊዮን ብር በማጭበርበር አውጥተው ሲያዘዋውሩ የነበሩ ተጠርጣሪ ግለሰቦችም መያዛቸውን የፖሊስ ኮሚሽን በአስታውቋል፡፡ግርማይ ንጉሴ ተክላይ እና ያዘው ክበበው ወርዶፋ የተባሉ ተጠርጣሪ ግለሰቦች ገዛኢ አድሃኖም በእጣ በተባለ ግለሰብ ስም በተከፈተ የቁጠባ ሂሳብ ደብተር ውስጥ ከተቀመጠ 40 ሚሊዮን ብር መቀሌ የወጣ መንጃ ፍቃድ ይዘው ጎላጎል አካባቢ ከሚገኘው አንበሳ ኢንርናሽናል ባንክ በመቅረብ 13 ሚሊዮን ብር አውጥተው እዚያው ባንኩ ውስጥ በግርማይ ንጉሴ ተክላይ ስም በተከፈተ የባንክ ደብተር በማዘዋወር ላይ እያሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
እጅ ከፍንጅ ከተያዙት ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ጋርም የአንበሳ እና የአቢሲኒያ ባንክ ያልተፃፈባቸው ቼኮች፣ ልዩ ልዩ የባንክ ደብተሮች፣ ሶስት ኤቲ ኤሞች በኤግዚቢትነት መያዛቸውን ፖሊስ ኮሚሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት በርካታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እያዋለና ሴራቸውን እያከሸፈ ያለው ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት መሆኑንም አስታውቋል፡
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።