በአዲስ አበባ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ 6 ሺህ ጥይቶች እና 98 ሽጉጦች ተያዙ ። በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ተሽከርካሪዎች ተጭነው በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 6ሺህ ጥ...

በአዲስ አበባ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ 6 ሺህ ጥይቶች እና 98 ሽጉጦች ተያዙ ። በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ተሽከርካሪዎች ተጭነው በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 6ሺህ ጥይቶች እና 98 ሽጉጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ከህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ ክትትል ሲደረግበት የነበረው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2- 95974 አ.አ የሆነ ተሽከርካሪ ከቦሌ ቡልቡላ ወደ ቦሌ ሚካኤል እየተጓዘ ወረዳ 05 ሚሊኒየም ፓርክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲደርስ በአዲስ አበባ ፖሊስ እና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ቅንጅት በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡ በተሽከርካሪው ላይ በተደረገ ፍተሻም 58 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ፣ 1ሺህ 988 የብሬን፣1ሺህ 286 የክላሽ፣ 1ሺህ 576 የሽጉጥ እና 154 የሌሎች መሳሪያዎች ጥይቶች በማዳበሪያ ተጠቅልለው ተይዘዋል፡፡ ከተያዙት የሽጉጥ ጥይቶች መካከል የተወሰኑት በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት በብርበራ የተገኙ መሆናቸውን የጠቀሰው ፖሊስ 1 ገጀራ፣ 2 ጩቤ፣ 2 የክላሽ ካርታና 1 ወታደራዊ ትጥቅ መያዣ ቀበቶ በፍተሻው በተጨማሪነት መገኘታቸውን አስታውቋል፡፡ በተመሳሳይ ሐምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2- A00243 አ.አ የሆነ ተሽከርካሪ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ሲደርስ በአዲስ አበባ ፖሊስ እና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ቅንጅት በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡ በተሽከርካሪው ላይ በተደረገ ፍተሻም 40 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ እና 996 የብሬን ጥይት የኋላ ኮፈን ውስጥ ተደብቆ መገኘቱን ያስታወቀው ፖሊስ ከተሽከርካሪው የኋላ ወንበር ጀርባ የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ዕቃዎችን ለመደበቅ የሚያገለግል ዘዴ ተዘጋጅቶ መቀመጡን ጠቅሷል፡፡ በቁጥጥር ስር በዋሉት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተጣራ ሲሆን የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ተሽከርካሪቸውን በውሰትም ሆነ በኪራይ ለሌላ ሰው አሳልፈው በሚሰጡበት ወቅት ተመሳሳይ ወንጀል ሊፈፀምበት እንደሚችል በመገንዘብ አስፈላጊውን ክትትል እና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

Share this Post