በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች እና ተማሪዎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እና አሸባሪው የሕውኃት ቡድን በከፈተው ጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አደረጉ።

 

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አስተባባሪነት ከመንግሥት እና ከግል ትምህርት ቤቶች የተሰበሰበውን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የአልባሳት ፣የንጽሕና መጠበቂያ፣ልዩ ልዩ የምግብ ዓይነትና የመማሪያ ቁሳቁሶች ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ርክክብ ተደርጓል ።

ሀገርን መውደድ በተግባር ሊገለፅ ይገባል ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተማሪዎች እና የትምህርት ማህበረሰቡ አባላት ከህፃን እስከ አዋቂ ያደረጉት ድጋፍም ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት የታየበት ነው ብለዋል።እኛም ለእናንተ ለልጆቻችን ሙሉ የግዛት አንድነቷን ያስጠበቀች ፤ የተከበረች፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት እየከፈልን ነዉ ያሉት ከንቲባዋ ለዚህም የትላንቱ ታሪክ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ዉሳኔ እና የጀግናው ሰራዊታችን ተጋድሎ ዋነኛ ማሳያ ነዉ ብለዋል።ጀግኖች አባቶች ለሀገር ክብር ሞተው የታፈረች ሀገር አውርሰውናል ፤ ኢትዮጵያ አትፈርስም የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ እና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵደያን ለቀጣይ ትውልድ እናወርሳለን ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ::ዛሬ ድጋፍ ላደረጋችሁ መላው ተማሪዎችን ፣ መምህራንን ፣ የተማሪ ወላጆችን ፤ አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ማህበረሰብ አካላትና አመራሮችን በራሴና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ድጋፉ በተደረገላቸዉ ወገኖቻችን ስም ከልቤ አመሰግናለሁ ብለዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ የትምህርት ማሕበረሰብ አባላት የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ከማድረግ ባለፈ የመከላከያ ሰራዊቱን ከደጀን እስከ ግንባር የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል ።ድጋፉ ከተማሪዎች ፣ ከመምህራን ፣ ከወላጆች እና ከትምህርት ዘርፉ አመራሮች የተሰባሰበ መሆኑን እና በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች ቦታው ድረስ በማድረስ እንደሚከፋፈል አቶ ዘላለም ተናግረዋል ::

 

 

Share this Post