በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ሰልጣኞች፣መምህራንና አመራሮች ለመከላከያ ሰራዊትና ለሌሎች የፀጥታ ሐይሎች ደም ለገሱ፡፡

 

በደም ልገሳ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክ ሙያ ፣ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን ሃብቱ ሀገራችን ከገባችበት አዘቅት ለማውጣት የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለመደገፍ የደም ልገሳ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ገልፀው ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ካለችብት ችግር እንድትወጣ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በእንጦጦ ፓሊ- ቴክኒክ ኮሌጅ በተካሄደው የደም ልገሳ መርሐግብር ከ300 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ኮሌጆች ሰልጣኝ ተማሪዎች፣መምህራንና አመራሮች ህይወቱን ለሀገሩ ህልውና እየሰጠ ለሚገኘው የመከላከያ ስራዊትና ለሌሎች የፀጥታ ሐይሎች ደም ለግሰዋል፡፡

ለሰራዊቱ ደም ከለገሱት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክ ሙያ ፣ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብርሃም ሰርሞሎ ከደም ልገሳ ባለፈ ኮሌጆችን በማስተባበር ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ የማሰባበሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከተለያዩ የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች የተውጣጡ ከ15 ባለሙያዎች እና ሰልጣኞች እንዲሁም 6 አመራሮች ለመከላከያ ሰራዊቱ የተሸከርካሪና ሌሎች የጥገና ስራ ላይ በሙያቸው ለማገልገል ወደ ግንባር ለመሸኘት ዝግጀት እየተደረገ መሆኑን ምክትል ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም በከተማዋ ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች የተውጣቱ ሰልጣኞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በሙያቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ አብርሃም ሰርሞሎ ተናግረዋል፡፡

Share this Post