በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ መርሐግብር በጣሊያን ሮም ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የዓለም ስነ ምግብ ኮንፈረንስ ላይ በተሞክሮነት ቀረበ፡፡ በተባበሩት መንግስታት...

በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ መርሐግብር በጣሊያን ሮም ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የዓለም ስነ ምግብ ኮንፈረንስ ላይ በተሞክሮነት ቀረበ፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዘጋጅነት በጣሊያን ሮም ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የስነ ምግብ ስርዓት ኮንፈረንስ የድርጅቱ ዋና ጽሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝንን ጨምሮ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፤ የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴንና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ተሳትፈዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በምገባ ዘርፍ የጀመራቸው ስራዎች ለሌሎች ሀገራትም ምርጥ ተሞክሮ እንደሚሆን በማመን የዓለም ምግብ ኮንፈረንሱ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የስነ ምግብ ዘርፍ አማካሪ ወ/ሪት ሜቲ ታምራት በከተማው እየተከናወነ ያለውን የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ተሞክሮን ከአዲስ አበባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በባለፈው በጀት ዓመት ለትምህርት ምገባ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ በከተማዋ እና በዙሪያዋ ለሚገኙ ከ600ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የስነ ምግብ ዘርፍ አማካሪዋ አብራርተዋል። በዚህም ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የተማሪዎችን ወጤት በማሳደግ ፤ የመድገምና የማቋረጥ ምጣኔን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል ብለዋል። በምገባ ፕሮግራሙ ምግብ በማብሰል ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እናቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ቋሚ ገቢ እንዲያገኙ መደረጉ መቲ ታምራት ገልፀዋል። በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለያዩ 5 ክፍለ ከተሞች በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በመለየት የምግብ አገልግሎት እንዲያገኙ የመመገቢያ ማዕከላትን በማቋቋም በሺዎች የሚቆጠሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችላል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያም የምግብ ስርዓት ለማሻሻል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የመንግስት አጀንዳ ሆኖ እየተሰራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትሯ ዶ /ር ሊያ ታደሰ በዓለም የስነ ምግብ ኮንፈረንስ አቅርበዋል ::

Share this Post