በድሎች ባለመዘናጋት አንድነትን አስጠብቆ ለላቀ ድል በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ተጠቆመ።

 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ የተገኘውን አገራዊ ድል ዘላቂ በማድረግ ብልፅግናን እውን ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ጋር ተወያዩ።

የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት አሸባሪው ህወሐት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ጦርነት መክፈቱን በማስታወስ በሞራልና በስንቅ ብቻም ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ በመዝመት የጋራ ድል መጎናፀፉን አስረድተዋል። በአንድነት ከቆምን የማያሸንፉት ሀይል አለመኖሩን በታሪክ በአድዋ የሚያወሱት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ዛሬም እያስመሰከሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችንና የዘማች ቤተሰቦችን በማቋቋም እንዲሁም የወደሙ ንብረቶችን በጋራ በመገንባት በድህረ ጦርነት ድላችንን አስጠብቆ መዝለቅ እንደሚገባ ከንቲባዋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ ኢትዮጵያን ለማዳን ሁሉም መክፈል ያለበትን መስዋዕትነት ለመክፈል በመቁረጡ ጦርነት የሚያስከትላቸውን ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ተቋቁመን ለሌላ ድል በጋራ ቁመናል ብለዋል።

ወቅቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አቅምና ጀግንነት በፈተናወች ዳብሮ የወጣበት እንዲሁም የአመራርና የህዝብ ቅንጅታዊ ስራዎች ከመቸውም ጊዜ በላይ ጎልቶ የወጣበት መሆኑን አቶ መለሰ አስገንዝበዋል። አመራሩ በጥብቅ ዲሲፕሊንና በሀገር ፍቅር በተጀመረው የህዝብ ድጋፍ የአዲስ አበባንም የኢትዮጵያንም ብልፅግና እውን ለማድረግ ሌት ተቀን እንደሚተጋም አረጋግጠዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደገለጹት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በዲሞክራሲያዊ ባህል ግንባታና ህዝባዊ አንድነትን በመገንባት ለኢትዮጵያ ካበረከቱት የላቀ ተግባር በተጨማሪ ግንባር ድረስ በመዝመት ለአገርና ለህዝብ መኖርን በተግባር አሳይተውናልና አርአያቸውን ተከትለን ሁሌም ከጎናቸው እንቆማለን የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

መስዋዕትነትን የከፈለልንን መከላከያ ሰራዊታችን በዘላቂነት ድጋፋችን አይለየውም ያሉት የውይይቱ ተሳታፊወች ለአንድም ቀን ሳንዘናጋ አካባቢያችን እንጠብቃለን፣ እናለማለን የሚሉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

Share this Post