02
Aug
2021
ባለስልጣኑ ከ 422 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የግንባታ ግብዓቶችን በ2013 በጀት ዓመት ማምረቱን ገለፀ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በተጠናቀቀው 2013 በጀት ዓመት ውስጥ ለመንገድ ግንባታ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ከ422 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ለተለያዩ የግንባታና የጥገና ስራዎች ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉን አስታወቀ፡፡ ባለስልጣኑ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ካመረታቸው የግንባታ ግብዓቶች መካከል 142 ነጥብ 80 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የካባ ምርቶች፣ 85 ነጥብ 54 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የሲሚንቶ ውጤቶች እና 193 ነጥብ 88 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የአስፋልት ኮንክሪት ውጤቶችን በራሱ ዓቅም አምርቶ ለተለያዩ የግንባታና ጥገና ስራዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ አድርጓል፡፡ ባለስልጣኑ በ2013 በጀት ዓመት ውስጥ ያመረታቸው የግንባታ ግብዓቶች ከ2012 ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀሩ የ 5 ነጥብ 8 በመቶ ብልጫ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡ የግንባታ ግብዓቶቹ በራስ ዓቅም መመረት መቻላቸው ባለስልጣኑ እያከናወናቸው ለሚገኙ የተለያዩ የግንባታና የጥገና ስራዎች የግብዓት እጥረት እንዳይፈጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ባለስልጥኑ ገልፆል፡፡