ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ላደረጉ የአፍሪካ የኤዢያና ፓስፊክ ሀገራት አምባሳደሮች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ተደረገ ።

 

በዉይይት መድረኩ የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነዓ ያደታ የከተማዋን ሰላም እና መረጋጋት ለማስቀጠል የከተማው የፀጥታ ሀይል ከፌዴራል ፖሊስ ፣ ከሪፐብሊካን ጥበቃ ሃይል ፣ከኦሮሚያ ፖሊስ እና ከሌሎች የፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

ከ27 ሺህ በላይ ወጣቶች እና ህዝባዊ ሰራዊት የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታን የሚያስከብሩ አደረጃጀቶች እስከ ታችኛው የብሎክ መዋቅር ድረስ በመደራጀት ወደ ስራ መግባታቸውን የገለጹት ዶ/ር ቀነዓ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በአስተማማኝ ሰላም ላይ መሆኗን አንስተዋል ።

በምዕራባዊያን ሚዲያዎች የሚነዙትን የፕሮፖጋንዳ እና የሽብር ወሬ መሬት ላይ ካለዉ የከተማዋ የተረጋጋ ሰላም ጋር ፍፁም የሚጋጭ በመሆኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ምንም አይነት ስጋት እንዳይገባው የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊው ዶክተር ቀነዓ ያደታ ገልጸውላቸዋል ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የስራ፣የኢንተርፕራይዞች እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው በቀጣይም ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ከተማ ካደረጉ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መሰል ወይይቶች ፤ የግንኙነት መድረኮችን በመፍጠር ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።

በሁለንተናዊ መልኩ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ህዝባዊ የፀጥታ አደረጃጀቶችን በማሰልጠን በሁሉም ወረዳዎች በማሰማራት እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራትና የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች ዙሪያ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ሰፊ ማብራሪያ እና ገለፃ በመስጠት የተሟላ መረጃ እንዲኖራቸው ተደርጓል ።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ

 

Share this Post