ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን የህልውና ጦርነት በድል እንድትወጣ ለመከላከላከያ ሰራዊቱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ የከተማ አርሶ አደሮች ላበረከቱት አስተዋጽአ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋና አቀረቡ፡፡

 

በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከከተማዋ አርሶ አደሮች ጋር ውይይት ተካሂዷል ፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለመከላከያ ሰራዊቱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግና የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ከማስጠበቅ በተጨማሪ ልጆቻቸውን ወደ ግምባር መርቀዉ በመላክ ሀገራችን ተገዳ የገባችበትን የህግ ማስከበር የህልውና ጦርነት በድል እንድትወጣ የከተማዋ አርሶ አደሮች ታሪክ የማይረሳው አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ታሪክ ሳናበላሽ ፤ ታሪካችንን በደማቅ ቀለም ጽፎ እና የማይሞት ታሪክ ሰርቶ ማለፍ ትልቅ እድል ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለዚህ ደግሞ የከተማ አርሶ አደሩ የአዲስ አበባን ዙሪያ በንቃት በመጠበቅ እንዲሁም ለአገር መከላከያ ሰራዊቱ እያደረጉት ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት የከተማዉ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ከከተማዋ ከንቲባ የቀረበላቸውን የእናት አገር ጥሪ በመቀበል ኢትዮጵያ ወደ ተረጋጋ ሰላም እስክትመለስ ድረስ ከመንግስትና ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመሆን የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ ገልጸው ለመከላከያ ሰራዊቱና ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርጉትን ድጋፍ ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም በአቋም መግለጫቸዉ ተናግረዋል ፡፡

Share this Post